የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በደባይ ጥላት ግን ወረዳ ናብራ ሚካኤል ቀበሌ ያስገነባውን የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት አስመረቀ

  • -

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በደባይ ጥላት ግን ወረዳ ናብራ ሚካኤል ቀበሌ ያስገነባውን የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት አስመረቀ

Print Friendly, PDF & Email

 

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ (ደ.ማ.ዩ)፡- ሰኔ 07/2014 ዓ.ም (ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዲሬክቶሬት) የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታውን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት ሞላልኝ ታምሩ (ዶ.ር) እና የደባይ ጥላት ግን ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሰዋለ መኮነን በጋራ መርቀው የከፈቱት ሲሆን በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ የዩኒቨርሲቲያችን አመራሮች፣የወረዳው የቢሮ ሃላፊዎችና የቀበሌው ኗሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በዕለቱም ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ደምሳቸው ሽታው እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲያችን 395 ሺ 500 ብር በመመደብ ለናብራ ሚካኤል ቀበሌ ማህበረሰብ የሰውና የእንስሳት መጠጥ ውኃ ገንብቶ ለማስረከብ ችሏል፡፡ ይህ የንፁህ መጠጥ ውኃ ከ300 በላይ ለሚሆኑ የቀበሌው ኗሪዎች፣ 1000 ለሚሆኑ ተማሪዎች እና ለ27 መምህራን አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልፀው በቀጣይ ይህን የንፁህ መጠጥ ውኃ በዘለቄታ ለማስቀጠል ያመች ዘንድ በአካባቢው የተፈጥሮ ሃብት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ እርክን መሰራት አለበት፣ ዛፍ መተክል አለበት እንዲህ ሲሆን ምንጮች ይጎለብታሉ የንፁህ መጠጥ ውኃው አቅርቦቱም እየጨመረ ይመጣል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ይህን ፕሮጀክት በአግባቡ እንዲሰራ ላደረጋችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኃል በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

በመጠጥ በውኃ ምርቃቱ ላይ ተገኝተዉ ሀሳባቸውን የሰጡት የናብራ ሚካኤል ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ ውበት እንደገለፁት የናባራ ሚካኤል ቀበሌ ማህበረሰብና እንስሳት ለዘመናት በውኃ እጦት ችግር ዉሥጥ ኖሯል፡፡ በቀበሌው የሚኖሩ መምህራን፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ የጤና ባለሙያዎች ተማሪዎች፣ በውኃ ጥም ሲገረፉ ኖረዋል ይህም በትምህርታቸውና በስራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም ውኃ ፍለጋ ሁለትና ሶስት ኪሎሜትር በመሄድና በአህያ በመጫን ንፅህናው ያልተጠበቀ ውኃ ሲጠቀሙ መቆየታቸውን ጠቅሰው አሁን ግን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ይህን ከፍተኛ የሆነ የውኃ ችግር በመገንዘብ ለሰውና ለእንስሳት የንፁህ መጠጥ ውኃ ገንብቶ ለማህበረሰቡ በማስረከቡ ምስጋናዬ ይድረሰው ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ ሀሳባቸውን የሰጡት መምህርት ለወየሁ መላኩ እንደገለፁት ከዚህ በፊት ውኃ ለማግኘት ብዙ ርቀት ለመሄድ እንደሚገደዱና ይህም በስራቸው ላይ ችግር ፈጥሮባቸው እንደቆየ ገልፀው አሁን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶ የንፁህ መጠጥ ውኃ ገንብቶ ለማህበረሰቡ በማስረከቡ ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ምርቃት ላይ ተገኝተው ሀሳባቸውን የሰጡት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ መልካሙ በዛብህ (ዶ.ር) እና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ድርቧ ደበበ (ዶ.ር) የዩኒቨርሲቲያችን መለያ መርሆው ”የዕውቀት አውድማ ከጮቄ ማማ“ እንደመሆኑ መጠን የዛሬ ፕሮጀክት ለዚህ መርሆዋችን አንዱ ማሳያ ተግባራችን ነዉ ብለዋል፡፡ በቀጣይም ይህ ዛሬ የተመረቀዉ ዉሃ ፕሮጀክት ለማህበረሰቡ ፍትሃዊ ተደራሽነት እንዲኖረው፣ የፀብ ምንጭ እንዳይሆንና ማህበረሰቡ የራሱ ሃብትና ንብረት መሆኑን አውቆ በአግባቡ እንዲጠቀም እንዲሁም እንዲጠብቀው ማድረግ ይኖርባችኋል በማለት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከማህበረሰቡ የወጡ ምሁራን የአካባቢያቸውን ችግር ነቅሰው በማውጣት እንዲህ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረት በማድረጋቸው፤ የአካባቢው ማህበረሰብም ለተግባራዊነቱ በጉልበትና በገንዘብ ላሳየው ተነሳሽነት ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር ሊመሰገኑ እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡  


Search DMU

Upcoming Events

There are no upcoming events.

Partners

DMU Radio Broadcasting . . .