የ2ኛውን ዓይነት የስኳር በሽታ ቁጥጥርን በተመለከተ ውጤታማ የሆነ ተግባራዊ ተሞክሮ

  • -

የ2ኛውን ዓይነት የስኳር በሽታ ቁጥጥርን በተመለከተ ውጤታማ የሆነ ተግባራዊ ተሞክሮ

Print Friendly, PDF & Email

 

ስሜ ዶ/ር ዘውዱ ወንዲፍራው እባላለሁ፡፡ በሙያዬ በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር ነኝ፡፡ ላለፉት 5 ዓመታት የ2ኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ታማሚ ነበርኩ፡፡ በጥቅምት 2008 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ፣ በአንድ ሌሊት ከፍተኛ የሆነ የውሃ ጥም ስሜት፣ በተደጋጋሚ ሽንት መሽናት፣ የድካም ሰሜት፣ የአይን ብዥታ እና ትኩረት የማጣት ስሜት ተሰማኝ፡፡ እለቱ እንደጠባ ማለዳ ወደ ሆስፒታል ሄድኩና የደም ስኳር ምርመራ አደረግሁኝ ምግብ ሳልበላ 280 mg/dl ሆኖ አገኛሁት፡፡ እኔን የገረመኝ ነገር ከዚህ በፊት ስለ ስኳር በሽታ አንድም ቀን አስቤ አለማወቄ ነው፡፡ የበሽታው ምልክት በታየበት ወቅት የሰውነት ክብደቴ 82 ኪ.ግ. ነበር፡፡ ቁመቴ 1 ሜትር 65 ሴ.ሜ  ሲሆን የሰውነት ክብደት መረጃ ጠቋሚ ጋር ሲነጻጸር 30.12 ነበርኩኝ ማለት ነው ይህም በክብደት አመዳደብ ደረጃ መሰረት ከመጠን በላይ ክብደት ነበረኝ ማለት ነው፡፡ ከምርመራው በኋላ ሐኪሙ ሁለት አይነት በአፍ የሚወሰዱ መድሃኒቶችን ማለትም ሜቲፎርሚን እና ግሊቢንክላሚድ/ዳይኦኒል እንድወስድ አዘዘልኝ፡፡ የታዘዙልኝን መድሃኒቶች ለ 10 ተከታታይ ቀናት ወስጄ አቋርጥኩኝ፡፡ ምክንያቱም በአዕምሮዬ ለህይወት ዘመን የስኳር ህመምተኛ መሆንን በጭራሽ መቀበል አልቻልኩም፡፡

በምትኩ በሳምንት ለ 4 ሰዓታት መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት ጀመርኩ፡፡ በተጨማሪም ዝቅተኛ የሆኑ የሀይል ሰጭ ይዘት ያላቸውን ምግቦች ብቻ መመገብ ጀመርኩ እና በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ቁርስ መመገብ አቆምኩ፡፡ ማንኛውንም አልኮል እና ጣፋጭ መጠጥ መጠጣት አቆምኩ፡፡ በዚህ ምክንያት፣ በአሁኑ ወቅት የደም ስኳር መጠኔ ከ 280 mg/dl ወደ 103 mg/dl በአማካይ ተሻሽሏል፡፡ የሰውነት ክብደቴ በዚህ ጊዜ 65 ኪ.ግ ሲሆን ከመነሻ ክብደቴ 17 ኪ.ግ. ቀንሻለሁ፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ የቀንስኩትን የሰውነቴን ክብደት ሳይዋዠቅ በነበረበት ለማቆየት ችያለሁ፡፡

ከዚህ እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ስለ 2ኛው ዓይነት የስኳር በሽታ መጽሐፍትን እና ጥናታዊ ጽሑፎችን ከኢንተርኔት ማንበብ እንዲሁም ቪዲዮዎችን ከዩቲዩብ ማዳመጥ ጀመርኩ፡፡ እነዚህን ሁሉ መረጃዎች ከግምት በማስገባት 2ኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ሊድን እንደሚችል እና ብዙ ሰዎች መዳን እንደቻሉ ብዙ ማስረጃዎችን ለማየት ቻልኩ፡፡ በዚህ ረገድ ቶሮንቶ ካናዳ የሚገኘው ዶ/ር ጄሰን ፉንግ የ2ኛው አይነት የስኳር ህመምተኞችን ለማከም የተጠናከረ የአመጋገብ ስርኣት መጀመሩን ከበየነ መረብ ተረዳሁኝ፡፡ እርሱም በበሽታው ዙሪያ ህዝባዊ ንግግር ማድረጉን እና መፅሀፍትንም እንደፃፈ መረጃ አገኘሁ፡፡ እነዚህን መጻሕፍት ማለትም The Diabetes Code, The Obesity Code and The Complete Guide of Intermittent Fasting ከበይነመረብ ሰብስቤ አነበብኩ:: መጽሃፍቱም የዚህን አሰከፊ በሽታ መንስኤ ለመረዳት በጣም እረዱኝ፡፡ በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ዶ/ር ፉንግ ከመጠን በላይ የሰውነት ውፍረት ለ2ኛ ዓይነት የስኳር በሽታ ዋና መንስኤ እንደሆነ በዝርዝር ያስረዳል፡፡ ስለሆነም ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ውፍረት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚፈልግ ያምናል። እንዲሁም ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ውፍረት እና 2ኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ብዙ መመሳሰሎች እና ልዩነቶች እንዳሉት ያስገነዝባል፡፡ በመጽሐፎቹ ውስጥ ኢንሱሊን በሰውነት ክብደት ውስጥ ያለውን ማዕከላዊ ሚና እና የሰውነትን ክብደት ለመጨመር የኢንሱሊን የመቋቋም ችግር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተገንዝቤአለሁ፡፡ ስለሆነም እነዚህ መጻሕፍት የኢንሱሊን መጠንን በመቆጣጠር ከመጠን በላይ የሰውነትን ውፍረት ለመቆጣጠር እንደሚቻል ጠንካራ መረጃዎች ሰጠውኛል፡፡

የኢንሱሊን መጠንን ለመቀነስ በተለይም የስኳር እና የተጣራ እህልን ፍጆታ በመቀነስ የእሱን መመሪያዎች እከተላለሁ፤ እንዲሁም ጥሩ የፕሮቲን ደረጃ ያላቸውን ምግቦች መውሰድ ጀመርኩ እና ጤናማ የሆኑ ቅባቶችን ከበፊቱ መጠን በመጨመር መውሰድ ጀመርኩ። የእኔ የተመጣጠነ የካሎሪ መጠን ፍጆታ በየቀኑ መውሰድ የኢንሱሊን መቋቋም ችግር የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመቋቋም ውጤታማ መንገድ እንደሆነ ተረዳሁ እንዲሁም ጤንነቴን በማይጎዳ መልኩ ጠንካራ ጾም መጾም ጀመርኩ፡፡

አሁን ተለዋዋጭ የሆነ ፆም/ intermittent fasting/ እንደ ምርጥ የህክምና አማራጭ እጠቀማለሁ፡፡ ይህ ማለት በሳምንት ውስጥ 2 ቀን እጾማለሁ ማለትም አንድ የተመጣጠነ ምግብ በ 24 ሰዓታት ማለት ነው በዚህ ጊዜ ውሃና ስኳር የሌለው ሻይ/ቡና በማንኛውም ጊዜ እጠጣለሁ፡፡ በሌሎቹ 5 ቀናት ውስጥ ቁርስ መውሰዴን ሙሉ በሙሉ አቆምኩ ማለት ያለማቋረጥ የምጾመው 18: 6 ሰዓታት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እውነት ለመናገር በ52 አመቴ የ30 ዓመት ጎልማሳ እንደሆንኩ ያህል ብርታት ይሰማኛል፡፡ በየቀኑ ደስተኛ እና የበለጠ ዘና ያለ እና የበለጠ የአካል ብቃት ይሰማኛል።

ከዚህ በተጨማሪም በኒውካስል ዩኒቨርሲቲ የፕሮፌሰር ሮይ ቴይለር Life without Diabetes መጽሐፍን አንብቤያለሁ፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ለ2ኛው የስኳር በሽታ መንስኤው ለረዥም ጊዜ ከፍተኛ የካርቦሃይድሬት መጠን ፍጆታ በመኖሩ ምክንያት በጉበት እና በቆሽት አካላት ውስጥ ከፍተኛ የስብ ክምችት በመኖሩ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ስለሆነም ይህን በሽታ ለመቀልበስ በእነዚህ የአካል ክፍሎች የተከማቸው ስብ በእጅጉ መቀነስ መቻል እንዳለበት ያስረዳል፡፡

የእነዚህን ባለሙዎች ምክሮች በመከተል፣ በአሁኑ ጊዜ የእኔን 2ኛው ዓይነት የስኳር በሽታ በማጥፋት ደረጃ ላይ እገኛለሁ፡፡ ምንም አይነት መድሃኒት አልወስድም በየቀኑ የተስተካከለ አመጋገብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ብቻ፡፡

ዶ/ር ዘውዱ ወንዲፍራው

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ፣

የእንስሳት ሳይንስ ት/ክፍል፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር

Email: zewduwondifraw@gmail.com, Tele +251910172313


Search DMU

Upcoming Events

There are no upcoming events.

Partners

DMU Radio Broadcasting . . .