GROW WISER AT THE WATER TOWER
Staff Academic Administrative Graduate
ዩኒቨርሲቲያችን በመደበኛው፣ በተከታታይና በርቀት መርሐ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን በጠቅላላው 1ሺህ 20 ተማሪዎች የሴኔት አባላት፣ የተጋበዙ እንግዶችና መምህራን በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ አሰመርቋል። በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዚዳንት ሳይህ ካሳው (ዶ.ር) የ2016 በጀት አመት የስራ አፈፃፀም አጭር ሪፖርት እና የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በንግግራቸውም በተጠናቀቀው በጀት አመት በስኬት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ጠቅሰዋል። ከእነዚህም ውስጥ በሀገራችን በተለይም በክልላችን ውስጥ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በተፈጠረው የሠላም መደፍረስ ምክንያት ለተከታታይ ስድስት ወራት ምንም አይነት ትምህርት እንቅስቃሴ ሳይደረግ መቆየቱን አንስተው ከጥር ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ግን በተደረገ እንቅስቃሴ ከመላው ኢትዮጵያ የተቀበልናቸውን ወደ 26 ሺህ ተማሪዎች ቤት ተቀምጠው ከሚቆዝሙበት ሁኔታ አላቅቀን ወደ ግቢያችን እንዲገቡና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ጥሪ በማድረግ ያለምንም ችግር ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ የቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ አስችለናል ብለዋል። ይህም አጠቃላይ ከላይ እስከ ታች ያለው የዩኒቨርሲቲያችን ማህበረሰብ የጋራ ውጤት መሆኑን ግልፀው ሁሉንም አካላት አመስግነዋል።
ፕሬዚዳንቱ በመቀጠል እንደትልቅ ስኬት ያነሱት ጉዳይ ደግሞ በደህንነት ስጋት ውስጥም ሆነው ተመራቂ ተማሪዎች በመውጫ ፈተና ያስመዘገቡትን ከፍተኛ ውጤት ነው። በዚህም በመደበኛው መርሐ ግብር ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለመውጫ ፈተና ከተቀመጡት ተመራቂ ተማሪዎች ውስጥ 94% ያህሉ በማለፋቸው የተሰማቸውን ደስታ ጭምር ገልፀዋል።
በአጠቃላይ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አግልግሎት፣ በትብብርና አጋርነት እና በሌሎችም ዘርፎች በበጀት አመቱ የተከናወኑ አንኳር አንኳር ተግባራትን የዘረዘሩ ሲሆን በበጀት አመቱ የታዩ ችግሮችንም ጠቅሰዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ጌታሰው ከበደም በተማሪዎች ምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝቶ መልዕክት አስተላልፏል። በመልዕክቱም በቅድሚያ ተመራቂ ተማሪዎችን ለዚህች ልዩ ቀን በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ዩኒቨርሲቲ ማለት የትንሿ ኢትዮጵያ መሠረት ስትሆን አራቱም አቅጣጫዎች እርስ በርስ የተጋመድንበት እና አንዳችን ለአንዳችን እየተደጋገፍን ዕውቀትና የምንጋራበት ማዕድ መሆኗንም ጠቅሷል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ከየኮሌጆች ፣ ተቋማትና ት/ቤቶች ከ1ኛ-3ኛ ደረጃ ለያዙ የምስክር ወረቀት ፤ከየኮሌጆች ፣ ተቋማትና ት/ቤቶች 1ኛ ደረጃ ለያዙ ደግሞ የሜዳሊያ እንዲሁም በአጠቃላይ ከሴቶች 1ኛ ለወጣች ተማሪና ከአጠቃላይ ከግቢው 1ኛ ለወጣ ተማሪ የዋንጫ ሽልማት ሥነ ስርዓት ተካሂዶ የዕለቱ የምረቃ መርሐ ግብር ተጠናቋል።
There are no upcoming events.
DMU Radio Broadcasting . . .