በነፃ የህግ አገልግሎት ዘርፍ አበረታች ስራ መስራቱን ተገለፀ

  • -

በነፃ የህግ አገልግሎት ዘርፍ አበረታች ስራ መስራቱን ተገለፀ

Print Friendly, PDF & Email

ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በውስጡ ከያዛቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል አንዱ ነው፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ምህረት ዓለማየሁ የህግ ምክር አገልግሎት መስጠት፤ ቆሞ መከራከር፤ የክስ መልስ ማመልከቻ መፃፍና የህግ እውቀት ለፈለገ ሰው አጠቃላይ የህግ ትምህርት አገልግሎት መስጠት በነፃ የህግ አገልግሎት ዘርፍ የሚሰሩ ተግባራት እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ምህረት ገለፃ ነፃ የህግ ማማከር አገልግሎት ራሳቸውን ችለው መፃፍ፤ መከራከርና ጠበቃ ማቆም ለማይችሉና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች፤ አረጋዊያን፤ ሴቶች፤ ህፃናትና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሰጥ አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም የህግ እውቀት አገልግሎት ማግኘት ለሚፈልጉ ማንኛውም የህብረተሰብ አካላት እንደሚሰጥም አስረድተዋል፡፡

ይህ ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ከላይ የተጠቀሱት የማህበረሰብ ክፍሎች በሚገኙበትና ለጊዜው ዩኒቨርሲቲው በመረጣቸው ደጀን፤ ሉማሜ፤ አምበር፤ ረቡገበያ፤ አማኑኤል፤ ደንበጫ፤ ደብረ ማርቆስ ከተማና ደብረ ማርቆስ ማረሚያ ቤቶች እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡

እነዚህ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የተመረጡት አንዱ ከማህበረሰቡ በቀጥታ ጥቆማ ተሰጥቷቸው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከየኮሌጅ፤ ት/ቤቶችና ተቋማቱ ዩኒቨርሲቲው በለያቸው የትኩረት መስኮች መሰረት በባለሙያዎች ተለይተውና በዳሰሳ ጥናት ተጠንተው የሚቀርቡ እንደሆኑ ታውቋል፡፡

በዚህም ረገድ በ2010 ዓ.ም በሁሉም ነፃ የህግ ምክር አገልግሎት መስጫ ማዕከላት 71 ሰዎች ተጠቃሚ እንደሆኑ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ምህረት ዓለማየሁ ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በህግ አገልግሎት ዘርፍ የተጠቃሚዎችን የእርካታ ደረጃ ለመለካት ያልረካ፤ ዝቅተኛ፤ መካከለኛ፤ ከፍተኛና በጣም ከፍተኛ የሚሉ የእርካታ መመዘኛ መስፈርቶችን  አውጥተው እርካታቸው እየተለካ ቢሆንም አገልግሎቱ በተለያዩ ቦታዎች፤ የተለያየ ንቃተ ህሊናና የግንዛቤ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ስለሆኑ ሙሉ በሙሉ የእርካታ ደረጃቸውን ማወቅ  እንደማይቻል ተጠቁሟል፡፡ በቀጣይ ግን የእርካታ መለኪያውን በማዘመን የተሻለ ውጤትና ተሞክሮ ከተገኘና አስተማሪ ከሆነ በሌሎች ወረዳዎችም አገልግሎቱን በስፋት እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ከነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ባሻገር ማንኛውም ኮሌጅ፤ ተቋምና ትምህርት ቤት በየትኛውም ሙያ ጥያቄያቸውን ህጋዊ አድርገው ቢያቀርቡ ዳይሬክቶሬቱ ሊያግዝና አገልግሎቱን በቅንነት ሊሰጥ ዝግጁ እንደሆነ ገልጿል፡፡


Search DMU

Upcoming Events

There are no upcoming events.

Partners

DMU Radio Broadcasting . . .