ከዞኑ በተመረጡ ተማሪዎች መካከል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ እና የሥነ-ጽሁፍ ውድድር ተካሄደ

  • -

ከዞኑ በተመረጡ ተማሪዎች መካከል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ እና የሥነ-ጽሁፍ ውድድር ተካሄደ

Print Friendly, PDF & Email

 

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው የልዩ ችሎታና ተሠጥኦ ማበልፀጊያ ማዕከል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ማላመድ እንዲሁም በስነ-ጽሁፍ ዘርፍ ከምስራቅ ጐጃም ዞን ትምህርት ቤቶች በተመረጡ ተማሪዎች መካከል ውድድር አካሄደ፡፡

በውድድሩ ወቅት የተገኙት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ ወንድይፍራው የማዕከሉን ዓላማ አብራርተዋል፡፡ የልዩ ስጦታና ተሰጥዖ ማዕከሉ የተቋቋመበት ዓላማ ተማሪዎች የሚማሩትን ትምህርት ወደ ተግባ በመቀየር ያላቸውን ልዩ ተሰጥዖና ችሎታ አውጥተው አዳዲስ ፈጠራዎችን መፍጠር እንዲችሉና የተመራማሪነት አቅማቸውን ለማሳደግ ነው ሲሉ ዶ/ር ዘውዱ ተናግረዋል፡፡ ወቅቱ የሚፈልገውን የቴክኖሎጂና ፈጠራ ችሎታ ያለው የሠው ሃይል ለማግኘት ብሎም ከፍተኛ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት እንደዚህ ዓይነት የውድድር መድረኮች የሚሰጡት ጠቀሜታ  ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ችሎታና ተሠጥዖ ማበልፀጊያ ኦፊሰር አቶ ገበየሁ ሽፈራው  ውድድሩ የተዘጋጀው በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በስነ-ጽሁፍ ዘርፎች ስለሆነ ለተማሪዎች መልካም አጋጣሚዎች ይፈጥርላቸዋል ብለዋል፡፡ በዚህ ውድድር የማወዳደሪያ መስፈርቶችም የፈጠራው ችግር ፈችነት፣ ከአሁን በፊት ያልተሠሩ መሆኑ፣ ተወዳዳሪዎች ለሚነሡ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልስ አሳማኝነት፣ ከየተሰሩባቸው ቁሳቁሶች እና ለተሠራው ስራ ማብራሪያ የመስጠት ችሎታን  የያዙ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡

በዚህ ውድድር ከአዋበል ወረዳ ሉማሜ ቁጥር አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣው ተማሪ ዮሐንስ መኩሪያው አሸናፊ ሆኗል፡፡ ተማሪ ዮሐንስ ይዞት የመጣው የጥያቄና መልስ ውድድር ውጤት ማሳወቂያ ዲስፕሌይ ማሽን ሲሆን ማሽኑን ሙሉ በሙሉ ከአካባቢው ካገኛቸው ቁሳቁሶች እንደሰራቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘመኑ ታረቀኝ በበኩላቸው ዝግጅቱ ተማሪዎች እምቅ ችሎታቸውን አውጥተው ወደ ተግባር የሚቀይሩበት፣ ጥሩ የፈጠራ ስራዎች የሚወጡበት፣ የማህበረሠቡን ችግር የሚፈቱ የፈጠራ ሥራዎች የሚፈልቁበት እንዲሁም ለስነ-ፅሁፍና ሥነ-ጥበብ ዕድገት እምርታ የሚመጣበት ነው ብለዋል፡፡

በውድድሩ በ11 ወረዳዎች ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን በልዩ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች ለሌሎች ሞዴል መሆን እንዳለባቸው ተገልጿል፤ ለፈጠራ ሥራቸው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት ረገድም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ አቶ ዘመኑ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማዕከልም ተመሳሳይ ውድድሮችን በያመቱ አዳዲስ የፈጠራና የልዩ ተሰጥዖ ባለቤት የሆኑ ታዳጊዎችን መድረክ በማዘጋጀት ዕውቅና ይሰጣል፡፡


Search DMU

Upcoming Events

There are no upcoming events.

Partners

DMU Radio Broadcasting . . .