የአመራር ፎረም አባላት የቡሬ ካምፓስ የግንባታ ስራዎችን ጎበኙ

  • -

የአመራር ፎረም አባላት የቡሬ ካምፓስ የግንባታ ስራዎችን ጎበኙ

Print Friendly, PDF & Email

 

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቡሬ ካምፓስ የህንፃ ግንባታዎች የስራ እንቅስቃሴ በዩኒቨርሲቲው የአመራር ፎረም አባላት ተጎበኘ፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ ልማት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳይህ ካሳው የጉብኝቱን ዓላማ ሲያስረዱ በመገንባት ላይ ያሉ አስራ አንድ ህንፃዎችን የአማካሪ ድርጅቱ ስራ አስኪያጅና የተቋራጭ ድርጅቱ ተቆጣጣሪ መሃንዲስ በተገኙበት ርክክብ ከመፈፀሙ በፊት ጉብኝት መደረጉ በአመራር ፎረሙ አባላት አስተያየት ተሰጥቶበት የታዩ ችግሮች ካሉ  ከወዲሁ ለማስተካከል እንዲያመች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ህንፃዎቹ ስራ ከመጀመራቸው በፊት መሰረተ ልማት ለማሟላት ጨረታ የማውጣት ስራ እየተሰራ መሆኑና በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ስራ እንደሚጀምር ገልፀዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የአማካሪ ድርጅቱ አማካሪ መሀንዲስ አቶ ዮናስ ሙሉሰው ለተሳታፊዎች የግንባታውን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በሪፖርቱም  ግንባታው በ956 ቀናት እንደተጠናቀቀ በመግለፅ ግንባታው የመማሪያ ክፍሎች፤ የተማሪዎች ዶርምተሪ እና መመገቢያ አዳራሽ እንደያዘና ሶስት ዓይነት አማራጭ የሀይል ምንጮች የተሟሉ ሲሆን ጥራታቸውን የጠበቁ ከመሆናቸው ባሻገር ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሆነው እንደተሰሩ አስረድተዋል፡፡ እስካሁን ድረስም ለግንባታው ከ374 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል በማለት ተናግረዋል፡፡ ቀሪ ስራ የማፅዳት ስራ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ርክክቡ እንደሚካሄድ አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሳይት ወርክ ስራ፤ የሶላር መሳሪዎች አቀማመጥና የመሰረተ ልማት ስራዎች አለመሟላት የሚታዩ ችግሮች እንደሆኑ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን አማካሪ መሀንዲሱ አቶ ዮናስ ሙሉሰው ከተቋራጭ ድርጅቱ ጋር በመነጋገር የማስተካከል ስራ የሚሰራ ሲሆን የሳይት ስራ ግን በአዲስ ውል ስለሚሰራና የውሉ አካል ስላልነበረ እንዳልተጠናቀቀ አብራርቷል፡፡

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች ግንባታው በጥሩ ሁኔታ እንደተከናወነ ገልፀው ያልተጠናቀቁ ስራዎች በቶሎ ቢጠናቀቁና በመማሪያ ክፍሎች የውሃ አገልግሎትና የመፀዳጃ አገልግሎት እንዲሁም ስራ ከመጀመሩ በፊት የግቢ ዋና ዋና መንገዶች እንዲሟሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡


Search DMU

Upcoming Events

There are no upcoming events.

Partners

DMU Radio Broadcasting . . .