ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ከደብረ ማርቆስ ከተማ አመራሮችና ነዋሪዎች ጋር ምክክር አደረገ፡፡

  • -

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ከደብረ ማርቆስ ከተማ አመራሮችና ነዋሪዎች ጋር ምክክር አደረገ፡፡

Print Friendly, PDF & Email

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች የ2012 የትምህርት ዘመንን ሰላማዊ ለማድረግ እና  ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ነባርና አዲስ ተማሪዎችን  በአግባቡ ለመቀበል ከደብረ ማርቆስ ከተማ  አስተዳደር  አመራሮች እና ከከተማው ነዋሪዎች ጋር በዩኒቨርሲቲው ዮፍታሄ ንጉሴ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አካሄዱ፡፡

የደብረ ማረቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ ከምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና ስተዳዳሪ አቶ አብርሀምና የደብረማረቆስ   ከተማ ምክትል ክንቲባ አቶ ይትባረክ ጋር ውይይቱን ሲመሩ

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንተ ዶ/ር ታፈረ መላኩ የ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን   ሰላማዊና የተረጋጋ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ የቆዩትም ሆነ  በአዲስ ተመድበው  ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ተማሪዎች  የመጡለትን አላማ  በአግባቡ አሳክተው  እንዲመለሱ ለማድረግ  የአካባቢው ማህበረሰብ  ከዚህ ቀደም ሲያደርገው የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ እነዲቀጥልም ዶክተር ታፈረ አደራ ብለዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ   በ2011 ዓ.ም   ዩኒቨርሲቲው  ከከተማው ነዋሪዎች  ጋር በጋር የነበሩ ሁኔታዎች  ላይ  በመወያየት  ያጋጠሙን ችግሮችን  በአጭር ጊዜ  በመቀልበስ  ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲፈጠር  ስላደረጉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የ2012  ዓ.ም የትምህርት  ዘመንን  ሰላማዊ  ለማድረግ  በመማር ማስተምሩ ዘጠኝ የቴክኖሎጅ ወርክ ሾፖችና 12 ቤተ ሙከራዎች መደራጀታቸውን፣  ከ25 ሚሊዮን  ብር በላይ  በሆነ ወጭ የመጽሀፍት ግዥ መፈጸሙን ፣የአይሲቲ መሰረተ ልማት ዝርጋታ መፈጸሙን  ፣ የመምህራን ቅጥር መፈጸሙን ፣የአንደኛ አመት የጋራ ኮርሶች ዝግጅት መደረጉን፣የመምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች  ውይይት መደረጉንና  በቀጣይ ለመምህራን  እና ለተማሪዎች የተለያዩ ስልጠናዎች  ለመስጠት መታቀዱን  ዶ/ር ታፈረ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የተማሪዎች  ምኝታ ክፍል  በሮችን በብረት  የመቀየር ፣ቀለም እንዲቀቡ  የማድረግና እንዲጸዱ ተደርጓል፡፡

እንዲሁም  የምግብ ጥሬ እቃዎች  ግዥ መፈጸሙን፣ የተማሪዎች  መዝናኛዎች እሰካሁን   ጥራታቸውን  የጠበቁ ስላልነበሩ ዩኒቨርሲቲው ያስገነባው  የተማርዎች መዝናኛ   በአጭር ጊዜ  ተጠናቆ  ወደ ስራ  እንዲገባ   እንደሚደረግም   ዶ/ር ታፈረ ተናግረዋል፡፡   ለሁሉም ተማሪዎች  አዲስ መታወቂያና  የመመገቢያ ካርድ  መሰራቱንና  በተለያየ ችግር ምክንያት  ከትምህርት የተሰናበቱ ተማሪዎችን  ወደ ግቢ እንዳይገቡና  የተለያዩ ችግሮችን እንዳይፈጥሩ  ለማድረግ  የታሰበ መሆኑን  ዶ/ር ታፈረ አክለው ገልጸዋል፡፡ ለችግር መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችንም አቅርበው  በዝርዝር  ሊሰሩ  በሚገቡ ጉዳዮች ላይ  ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሀም አያሌው የውይይቱ ዓላማ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሚፈጠሩ ችግሮች ለሌሎች ተቋማት ምክንያት እንዳይሆን የዩኒቨርሲቲው የቅድመ ዝግጅት  ሁኔታን  ማህበረሰቡ  እውቅና እንዲኖረውና የጎደሉት እንዲሟሉ ለማድረግና ሰላማዊ መማር ማስተማር   እንዲኖር ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ውይይቱ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ሰላምንና ደህነትን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ጉዳይ ላይ ክፍተት እንዳይኖረው  ያለው  ቅድመ ዝግጅትና ስጋቶችን  በተመለከተ፣ ከማህበረሰቡ  ምን ይጠበቃል በሚሉት ላይ ተወያይቶ ከባቢያዊ  በሆኑ ጉዳዮች ላይ  የስነ-ልቦና ዝግጅት  በማድረግ ወደ ስራ ለመግባትና  በጋራ ህግና ስር ዓትን ለማስከበር የሚያሰችል ውይይት  እንደሆነ አቶ አብርሀም አክለው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የባህሪ ችግር ያለበትን  ተማሪ  በማረምና በማስተካከል  ጥሩ ባህሪ እንዲኖረው  ማድረግ የአካባቢው  ማህብረሰብ  ትልቅ ባለ አዳራ  እንደሆነ አቶ አብርሀም ጠቁመዋል፡፡፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ  አቶ ይትበረክ አወቀ  ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ  ለደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች  ብቸኛው ኢንዱስትሪ በመሆኑ  ዩኒቨርሲቲውን  የመጠበቅ ሀላፊነት  ስላለብን  ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ  ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ወደ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለሚመጡ ተማሪዎች   የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች እንደ  ወላጅ በመሆን  እገዛ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ   ጠቁመው  የከተማ አስተዳደሩም የከተማውንና የዩኒቨርሲቲውን ደህንነትና  ሰላም ለመጠበቅ  በርካታ ዝግጅቶችን ማድረጉን አቶ ይትባረክ አክለው ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት ወደ  ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ  ተመድበው የሚመጡትም ሆኑ  ሲማሩ የቆዩት  ተማሪዎች   የማህበረሰቡ  ልጆች   በመሆናቸው ድጋፍ እና እገዛ እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል፡፡ የእኛም ልጆች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች   እየተማሩ ነው ያሉት ተሳታፊዎች  ልጆቻቸውን ለሌላው አካባቢ ማህበረሰብ   በአደራ እነደሰጡ ሁሉ  በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ  የሚማሩ ተማሪዎችም  የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች  የአደራ ልጆቻችን ናቸው  ብለዋል፡፡ ስለሆነም የመጡለትን ዓላማ አሳክተው እስኪሄዱ ድረስ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ተናግረዋል፡፡


Search DMU

Upcoming Events

There are no upcoming events.

Partners

DMU Radio Broadcasting . . .