አፈርን በኖራ በማከምና የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን በመጠቀም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ተገለጸ

  • -

አፈርን በኖራ በማከምና የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን በመጠቀም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ተገለጸ

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አሲዳማ አፈርንና ማምረት ያልቻለን መሬት ተፈጥሯዊ ስነ-ዘዴን በመጠቀም ማለትም ግብጦን ዘርቶ ስምንት ቅጠል እስኪያወጣ በመጠበቅና መልሶ በማረስና በኖራ በማከም መሬቱን መልሶ እንዲያገግም በማድረግና ምርጥ ዘርን በመጠቀም አርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነቱን በመጨመር የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል በምርምር የተገኘና ተግባራዊ የሆነ ስራ በመስራት 545 አርሶ አደሮችን በብቅል ገብስ የኩታ ገጠም እርሻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉ ተገለጸ፡፡

በስናን ወረዳ በደብረ ዘይት ቀበሌ በሜላትና በእነራታ የአርሶ አደሮች የኩታ ገጠም እርሻ የብቅል ገብስ  የሰብል ቁመና ከፌደራል፣ከክልል ከዞን፣ከወረዳ፣ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና ከተለያዩ የምርምር ማእከላት በመጡ የስራ ኃላፊዎች የመስክ ጉብኝት ከፊል ገጽታ

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደብረ ማርቆስ ግብርና  ምርምር ማዕከልና ከስናን ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በስናን ወረዳ ደብረ ዘይት ቀበሌ በሜላትና እነራታ ጎጦች በአሲዳማነት ምክንያት ማምረት ያልቻለን መሬት ሳይንሳዊ ዘዴን በመተግበር መሬቱን መልሶ እንዲያገግም በማድረግና የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን እንዲዘሩ በማድረግ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ ያስቻለ ስራ መስራቱን ጥቅምት 7 ቀን 2013 ዓ.ም በአርሶ አደሮች የመስክ ቀን በዓል ላይ በተደረገ የመስክ ጉብኝት ማረጋገጥ መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ሙላቱ ካሳዬ በአርሶ አደሮች የመስክ ቀን በአል ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማሩ ተማሪዎችን በተለያዩ ስልጠናና ትምህርት መስኮች ከመጀመሪ ዲግሪ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ በማሰልጠን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በማሰማራት ዜጎች የበኩላቸውን እንዲወጡ እያደረገ ያለ ተቋም መሆኑን በመጠቆም ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በጥናት ላይ ተመስርቶ የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶችንም እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለአካባቢው ማህበረሰብ እየሰጠ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በአካባቢው የሚስተዋሉ የአርሶ አደሩ ማነቆዎችን ለመፍታት የተለያዩ ችግር ፈች ጥናትና ምርምሮችን በመስራት ተጨባጭ የሆኑና ትርጉም ያላቸው በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናገረዋል፡፡

ዶክተር ሙላቱ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩ ችግር የሆነውን አሲዳማ አፈር ለማከምና የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በጥምረት የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀትና በማካሄድ እቅድ በማውጣት ወደተግባር በመግባት በተለያዩ የምስራቅ ጎጃም ወረዳዎች ማለትም በደብረ ኤሊያስ፤ በአዋበልና በስናን ወረዳዎች የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን መጨመር የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር እያደረገ ያለው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራም በዳቦ ስንዴ፤ በብቅል ገብስና በጤፍ ዝርያዎች ላይ መሆኑን አስታውሰው ዩኒቨርሲቲው በሌሎች የሰብል አይነቶችም ምርትና ምርታማነትን በሚጨምሩ፣ ድርቅን መቋቋም በሚችሉ፣ በሽታን በሚቋቋሙና በተለያዩ የደጋ ሰብሎች ላይ ምርምሮችን በመስራት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ተቀናጅቶ መስራትም ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም ከማስቻሉም በላይ ብክነትን ለማስቀረትና ድግግሞሽን በማስቀረት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ ኑሮው የሚለወጥበት፣ ግብርና የሚሻሻልበትና አካባቢንም ሆነ አገርን ማሳደግ የሚያስችል በመሆኑ በጥምረት መስራት ውጤቱ የላቀ መሆኑን በመግለጽ ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች አካላት ጋር በጥምረት ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነትና ዝግጁነት ዶክተር ሙላቱ ካሳዬ ተናግረዋል፡፡

በስናን ወረዳ ደብረ ዘይት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑትና የብቅል ገብስ የኩታ ገጠም እርሻ ተጠቃሚ የሆኑት አርሶ አደር ማናየ ውብእግዜር እና አርሶ አደር ወርቁ ተሾመ እንደገለጡት የእርሻ ቦታቸው በመራቆቱና ለምነቱን በማጣቱ ምክንያት ማምረት ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው የቆዩ መሆናቸውን አስታውሰው ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምርና ስናን ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በሰሩት ስራ መሬታቸውን አረንጓዴ ማዳበሪያ የሆነውን ግብጦ በመዝራትና ስምንት ቅጠል ካወጣ በኋላ መልሰው አርሰው በመገልበጥና በዩኒቨርሲቲው በተሰጠ የኖራ ድጋፍ በማከም መሬታቸው መልሶ አገግሞ አሁን ያለበትን የምርት ቁመና እንዲኖረው ማድረግ ያስቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ እንዳሉት ይህን ስራ የጀመሩት በ2011/12 የምርት ዘመን መሆኑን ጠቁመው በ2012/13 የምርት ዘመን ወደ ስራው ጠቅለው የገቡበት ባለፈው አመት የተሻለ ምርት  ማግኘት በመቻላቸው እንደሆነ ተናግረው ከዘንድሮውም በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲም እያደረገ ያለውን ድጋፍ በተለያዩ የሰብል ዝርያዎችና የእንስሳት እርባታ ላይ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አርሶ አደሮቹ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ማዕከልና ከስናን ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በስናን ወረዳ በሰሩት የብቅል ገብስና የዳቦ ስንዴ የኩታ ገጠም እርሻ የአርሶ አደሮች የመስክ ጉብኝት ቀን ከተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከኢትዮጵያ የግብርና ኢንስቲትዩት፣ ከምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ፤ ከስናን ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት፣ ከተለያዩ የግብርና ምርም ተቋማት፣ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸውና ተጋባዥ እንግዶች የጉብኝቱ ታዳሚዎች የነበሩ ሲሆን የእንኳን መጣችሁና ሌሎች በርካታ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡

በአብዛኛውም ዩኒቨርሲቲው እያደረገ ያለውን ስራ አድንቀው ተቋማት የብቻቸውን መቆም ሳይሆን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ትርጉም ያለው ስራ መስራት እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡ ለዚህም ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከምርምር ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ሊቀጥል ይገባል ተብሏል፡፡

በመስክ ጉብኝቱም ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ  የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ይሄይስ አረጉና የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ሙላቱ ካሳዬ ተሳትፈውበታል፡፡

Print Friendly, PDF & Email

DMU Radio Broadcasting . . .