Category Archives: News

  • -

“አድዋ የኢትዮጵያ የዘመናት የድል ብስራት ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ሃውልት ጭምር ነው፡፡ ሆኖም በተለያዩ ዘርፎች ሪከርዶች ይሰበራሉ በጦርነት ድል ግን የአድዋን ድል ሪከርድ ማንም ሊሰብረው አይችልም፡፡” ዶ/ር ታፈረ መላኩ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት

 

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ 126ኛውን የአድዋ ድል በዓል ‹‹አድዋ ለኢትዮጵያውያን ህብረት ለአፍሪካውያን የነጻነት ጮራ ›› በሚል መሪ መልዕክት በንጉስ ተክለሃይማኖት አደባባይ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የሐዲስ ዓለማየሁ የጉባዔ አዳራሽ በፓናል ውይይት ተክብሯል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት አድዋ  የኢትዮጵያ የዘመናት የድል ብስራት ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ሃውልት ጭምር ነው፡፡ ሆኖም በአትሌቲክሱ ዘርፍም ሆነ በሌሎች ዘርፎች  ሪከርዶች ይሰባበራሉ በአትሌቲክሱ  የአንዱን አትሌት ሌላኛው ወስዶታል የተመዘገበውን ውጤትም ሲያሻሽለው ተመልክተናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ  በጦርነት ድል ግን በዛ በማይመጣጠነው በአውሮፕላን መርዝ እየረጨ መድፍና ታንክ እያጓራ በቁመህ ጠብቀኝ በጋሻና ጦር ያንን ዘመናዊ የነጭ ወራሪ በስድስት ሰዓት ውስጥ ያሸነፈው ጥቁር ህዝብ ነው፡፡ የአድዋ ድል በየትኛውም ዘመን በጦርነት ድል ሪከርድ የማይሰበርበት  ድል ነው በዚህም ኩራት ይሰማናል፡፡ ለአባቶቻችን ለኢትዮጵያውያን ክብር ይገባል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምስራቅ፣ ከምዕራብ ከየአካባቢው ከጎጃም ፣ከሸዋ ፣ ከሀረር ከእያንዳንዱ አካባቢ ተጠራርቶ ዘረኝነት የለ ሁሉም ለአንድ አላማ ለሃገር ፍቅር ለሀገር ክብር በመዋደቃቸው በስድስት ሰዓት ውስጥ በማይታመን መንገድ ማሸነፍ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጅ ዛሬ ከአድዋ መማር የምንችለው  ፍቅር፣ ወንድማማችነት፣ፍጹም ኢትዮጵያዊ መሆን ይህ ሀገር ለማሳደግ፣ ሀገርን ወደ ወሳኝ መንገድ ለመውሰድ ትልቅ ስንቅ ሆኖ ያሉ ሲሆን ሌላው በተለይ ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ የሚማረው ነገር ቢኖር አንደኛው ፍጹም ኢትዮጵያዊነትን መገንባት ሁልጊዜ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በልቦናው ውቅር ውስጥ እንዲጎመራ ምንጊዜም መትጋት፡፡ ሁለተኛው የሀገር ፍቅር እስከ መስዋትነት ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የታሪክ መምህር  አቶ ግዛቸው አንዳርጌ (ረ/ፕ) “የኢትዮጵያ ህልውና እና የውጭ ጣልቃ ገብነት አድዋ እንደ ማሳያ” በሚል ርዕስ ለውይይት ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን  ሌላኛው የታሪክ መምህር  አየነው ማሞ (ዶ/ር)  “ለአድዋ ድል የአጼ ሚኒሊክ እና የእቴጌ ጣይቱ ሚና እና ለወጣቱ ያለው አስተምህሮ” በሚል ርዕስ  ጽሁፍ ቀርቦ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በድል በዓል አከባበሩ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በደብረ ማርቆስ ከተማ ወጣት ከያኒያን የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ለታዳሚዎች ቀርበው የአድዋን መንፈስ በመዘከር አስታውሰዋል፡፡


  • -

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችና ዲጅታል ቴክኖሎጅ ዙሪያ አውደ ውይይት ተካሄደ

 

የዛሬዋ ዓለማችን በደረሰችበት የእድገት ደረጃ ስልጣኔን ወይም ብልጽግናን ከቴክኖሎጂ ለይቶ ማየት ያስቸግራል። የሰለጠነ ህብረተሰብ ማለት ቴክኖሎጂን ያዳበረ ህብረተሰብ ማለት ነው። ባንጻሩም ቴክኖሎጂን ያላዳበረ ህብረተሰብ ማለት ደግሞ ያልበለጸገ ህብረተሰብ ነው። የሰለጠነ ህብረተሰብ ስንል ደግሞ ድኅነት የተረታበት፤ በሽታ የመነመንበት፤ ትምህርት የተስፋፋበት (እውቀት የለመለመበት)፤ ዲሞክራሲ የሰፈነበት፤ የመገናኛና ቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት በስፋት የተንሰራፋበትና ህግ የበላይ የሆነበት ህብረተሰብ ማለታችን ነው።

ቴክኖሎጂ እላይ ለተጠቀሱት ለሰው ልጆች አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ የሆነ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አለው። ይሄን ሲይደርግ ግን ቴክኖሎጂ ከህብረተሰብ ውጪ ሆኖ በታዓምር ወይም ትእዛዝ በመስጠት ሳይሆን በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የሚተገብሩት፤ ሌሎች የህብረተሰብ ምግባራትም ለምሳሌ ትምህርት፤ ኢኮኖሚ፤ ዲሞክራሲ በየፊናቸው ተጽእኖ የሚያደርጉበት ምግባር ነው።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት የፈጠራ ስራዎች ማበልፀጊያ ማዕከል በማቋቋም በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ነው፡፡ ዛሬ የካቲት 22/2014ዓ/ም ደብረ        ማርቆስንና  አካባቢውን በቴክኖሎጅ ለማበልጸግና በተለይም ደብረ ማርቆስ ከተማን “High Tech City” ለማድረግ ያለመ አውደ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ትምህርት በተግባር የህብረተሰባችን እና የራሳችን ህይወት እንዲቀይር መስራት ይኖርብናል ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) ቴክኖሎጂ ከተጽኖ ነጻ ያልሆነ ቢሆንም፤ እጅግ አስፈሪና አድካሚ የተፈጥሮ ጫናዎችን ያቀለለ፤ የችግሮች መፍቻ ቁልፍና ዘዴም ስለሆነ ተገቢው ትኩረት ከተሰጠው በተጽኖም ስር ሆኖ ህብረተሰባዊ ተልእኮውን መወጣት የሚያስችለው አቅም አለው። ይህም አቅም የሚመነጨው ቴክኖሎጂ ከችግር ፈቺነቱ በተጨማሪ ለፈጣሪው፤ አድራጊው ወይም ከዋኙ ለሆነው ለሰራተኛው ህዝብ አጋዥና ታዛዥ በመሆኑና ከዋኙና አድራጊው ደግሞ አብዛኛው ህዝብ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ለቴክኖሎጅ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ይደግፋል ብለዋል፡፡

በአውደ ውይይቱ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡትና በቴክኖሎጅ ዘርፍ ስራ ፈጣሪና የሶፍትዌር አበልፃጊ አቶ ሀብታሙ ቢያዝን  ቴክኖሎጅን መጠቀም የሀገር ውስጥ ችግርን ከመፍታት አልፎ ሶፍትዌርን በማበልፀግ እንደ ማንኛውም ዕቃ ወደ ውጭ በመላክ የገቢ ምንጭ ማድረግ እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡ አንዳንዴ የቴክኖሎጅ  ተግባራትን በመፍራት ፣በውጭ ሀገር ብቻ  እንደሚተገበር በማሰብ ራስን ማሳነስ  ሳይሆን በተግባር በመሞከር ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ጭንቅላትና ኮምፒውተርን በመጠቀም በአጭር ጊዜ በህይወታችን ለውጥ ልናመጣበት የምንችልበት ዘዴ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ገንዘብ ለማሰባሰብ፣ በበይነ መርብ  አማካኝነት የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን ፣ለተለያዩ የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት ተግባራቸውን ለማቀላጠፍ ያስችላል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግና ፋይናንስ መምህር ለጤናህ እጅጉ (ዶ/ር)  አዕምሮ ላይ ያለን ሀሳብ በማፍለቅ ወደ ቢዝነስ ለመቀየር የቢዝነስ ማበልፀጊያ ማዕከል ወሳኝ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዓለም ከደረሰበት ስልጣኔ ለመድረስ  ማንኛውንም ተግባር ዲጅታላይዝ በማድረግ ቀልጣፋ ተግባርን ማከናወን ይገባል በማለት ዘርፉ ቢዝነስ በመሆኑ ደብረ ማርቆስ እና አካባቢው ከሌላው ዓለም ጋር ሊወዳደርበት የሚችልበትን መልካም አጋጣሚ በመለየት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) ለሀሳቡ ተግባራዊነት በዩኒቨርሲቲ ደራጃ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በማሳሰብ ዩኒቨርሲቲው የሚሰጣቸው ተቋማዊ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቶች በዲጂታል የተደገፈ ቀልጣፋ አገልግሎቶች በሁሉም የስራ ክፍሎችና ተቋማት መዘርጋት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

በአውደ ውይይቱ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተማሪዎችና መምህራን የተሳተፉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስ ማበልፀጊያ ማዕከላትና በማዕከላቱ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጎብኝተዋል፡፡


  • -

ዓለማዊ ትምህርትና የኢትዮጵያዊያን ማያ መስተጋብር በሚል አውደ ውይይት ተካሄደ

 

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ “ዓላማዊ ትምህርትና የኢትዮጵዊያን ማያ መስተጋብር” በሚል ርዕሰ ጉዳይ አውደ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሰራተኞች እንዲሁም ተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡ በአውደ ወይይቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተወካይና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ይሄይስ አረጉ (ዶ/ር) ዛሬ ለውይይት የተመረጠው ርዕሰ ጉዳይ የትምህርት ተቋማት በየዓመቱ የሚያስመርቋቸው ወጣቶችና በትምህርት ተቋማት የሚገኘው ማህበረሰብ ዓለማዊ ትምህርትን ከኢትዮጵያ እሴትና ባህል አኳያ እንዴት እንደሚቃኝ እንዲሁም እንደ ሃገር ዓለማዊ የትምህርት ስርዓታችን ያፈራው ትውልድ ከኢትዮጵያዊነት ባህልና እሴት ያለውን ተዛምዶ ማያ ልናደርገው የሚገባ  ውይይት ይሆናል ብለዋል፡፡  “ዓላማዊ ትምህርትና የኢትዮጵዊያን ማያ መስተጋብር” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የውይይት መነሻ ፅሑፍ በወጣቶች ስነ-ምግባር ዙሪያ እና በግጭት አፈታት ዙሪያ አማካሪ የሆኑት ዓለም አቀፍ ምሑር አቶ ፈንታሁን ዋቄ ያቀረቡ ሲሆን በፅሑፋቸው ስድስት ያክል ጥያቄዎችን በማንሳት ተሳታፊዎችን ሞግተዋል ። ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከልም የኢትዮጵያ ዓለማዊ ትምህርት ስርዓትና ይዘት የሚመራበት ፍልስፍና ከየት አገኘው ? የማን ነው ? ለሰው ልጆች ማንነትና ለዓለም ያለው ርዕይ ምንድን ነው ?  እንዲሁም በተውሶና በሙከራ እውቀትና ርዕዮት አገርን አገር አድርጎ ማቆም ይቻላል ? የሚሉት ይገኙበታል፡፡

አቅራቢው አቶ ፈንታሁን ዋቄ የዘመኑን የማድነቅ ሳይሆን የሚቆነጥጥ አሉታዊ ወቀሳ ያለበት፤ ከምንገኝበት ምቾት በመውጣት ፅኑና ጥልቅ ጥያቄዎች በራሳችን ላይ ማንሳት ይኖርብናል በማለት ንጥል-ግንጥል የሆነ ዕይታ ሳይሆን ሁሉንም ማዕከል ያደረገ ተዋህዷዊ ዕይታን በማዳበር ግንዛቤና ህሊናን የሚያከበር ሁኔታን ለትውልዱ መፍጠር ይኖርብናል ያሉ ሲሆን ውጭን ብቻ የሚመለከት ምሑራዊነት ለአገራዊ ውድቀት ዋና መንስኤ በመሆኑ ወደ እራሳችን በመመለስ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ለሀገር ግንባታ መጠቀም ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በውይይቱ ከተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል ፡፡


  • -

ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች “የህይወት ክህሎት” ስልጠና ተሰጠ

 

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች ወጣቶች እና ኤች.አይ.ቪ /ኤድስ መከላከል ዳይሬክቶሬት ያዘጋጀው የህይወት ክህሎት ስልጠና በዩኒቨርሲቲው ለማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ፣ ለስነ-ትምህርትና ስነ-ባህሪ ተቋም እንዲሁም ለቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ሴት ተማሪዎች የተሰጠ ሲሆን ለስልጠና ተሳታፊ ሴት ተማሪዎች እና ለተጋባዥ እንግዶችን  የእንኳን ደህና መጣችህ በማለት ስለ ስልጠናው ገለፃ ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ሴቶች ወጣቶች እና ኤች.አይ.ቪ /ኤድስ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  ወ/ሮ ሰላም መክብብ እንዳሉት በዚህ የስልጠና መረሃ ግብር ላይ ዓረዓያ የሆኑ የዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን የህይወት ተሞክሮ እና ፣ የአቻ ግፊትን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ውይይት ይካሄዳል ብለዋል፡፡

በስልጠናው ላይ በመገኘት  በትምህርት ቆይታቸው ያሳለፉትን የህይወት ተሞክሮ ለተማሪዎች ያቀረቡት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህርትና የዩኒቨርሲቲው ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ድርቧ ደበበ (ዶ/ር ) እንዳሉት ተማሪዎች በትምህርት ቆይታችሁ በርካታ ፈተናዎች ሊገጥማችሁ ይችላል፤ ነገር ግን ይህን ፈተና በጥበብና በብልሃት ማለፍ ያስፈልጋል ፣ ይህን ካደረጋችኹ ልታሳኩት የምትፈልጉትን  ዓላማ በቀላሉ ማሳካት ይቻላል ያሉ ሲሆን ወጣትነት ብዙ ነገሮች የሚስተናገዱበት ነው ፤ ሁሉም ነገር በጊዜው ይደርሳል ፤ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም በሌላ በኩል ጓደኛን  መምረጥ፣ራስን መሆንና የአቻ ግፊትን መቋቋም አስፈላጊ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡  

በመጨረሻም የማጠቃለያ ሃሳብ የሰጡት በዩኒቨርሲቲው የአማረኛ ቋንቋና ስነ-ፅሁፍ ትምህርት ክፍል መምህርትና የስረዓተ ጾታ ተጠሪ ወ/ሮ ሀይማኖት እጅጉ እንደገለጹት ተማሪዎች የቤተሰብ አደራ አለባቹህ ፤ የሃገር አደራ አለባቹህ ስለዚህ ለመጣችሁበት ዓላማ ለራሳቹህ ታማኝ በመሆን ለጥሩ  ውጤት መብቃት ይጠበቅባችኋል  ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ሃሳብ ከሰጡት ተማሪዎች መካከል  የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት ስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ክፍል ተማሪ ቤተልሔም ማስረሻ እንዳለችው የሴቶች ወጣቶች እና ኤች/አይ/ቪ/ኤድስ መከላከል ዳይሬክቶሬት ስልጠናውን በማዘጋጀት እንድንወያይ፣ እንድንማማር ከሌሎች ዓረዓያ ከሆኑ ሴት መምህራን ተሞክሮ እንድንወስድ  መደረጉ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ሴት ተማሪዎችም በሴቶች ክበብ በንቃት መሳተፍ አለባቸው ፤ ስልጠናውና ውይይቱም ቀጣይነት ቢኖረው  በማለት ሃሳቧን ገልጻለች ፡፡

በመርሃ ግብሩ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የትያትርና ጥበባት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች አነቃቂ ድራማዎችን ለታዳሚዎች አቅርበዋል ፡፡


Search DMU

Upcoming Events

There are no upcoming events.

Partners

DMU Radio Broadcasting . . .