የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊና ነገረ-ሰብ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ አመታዊ ጥናት ምርምር ጉባኤ አካሄደ

  • -

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊና ነገረ-ሰብ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ አመታዊ ጥናት ምርምር ጉባኤ አካሄደ

ደ.ማ.ዩ፡- የደብረ ማርቆስ የኒቨርሲቲ ማህበራዊና ነገረ-ሰብ ኮሌጅ ከምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር  ዳይክቶሬት  ጋር በመተባበር “አዲስ ሀሳብ ለመልካም ስብዕና፣ለማህበረሰብ ለዉጥና ለሀገር ግንባታ” በሚል መሪ-ቃል ሚያዚያ 09-10/08/2013 ዓ.ም በንግስተ ሳባ እና በአለቃ ተክለኢየሱስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ አካሄዱ፡፡

በዕለቱ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊና ነገረ-ሰብ ኮሌጅ  ዲን ዶክተር አማረ ሰዉነት ሲሆኑ በንግግራቸዉም ማህበራዊና ነገረ-ሰብ ኮሌጅ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በስሩ ከአቋቋማቸዉ ኮሌጆች ዉስጥ የመጀመሪያዉ ኮሌጅ እንደሆነ በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያ ድግሪ፣ በሁለተኛ ድግሪ እና በሶስተኛ ድግሪ ፕሮግራም የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥናትና ምርምሮች እየጨመሩ በመምጣታቸውና ኮሌጆች ወቅታዊና አነጋጋሪ ጉዳዮችን እየለዩ ጉባኤዎችን እንዲያዘጋጁ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት በማህበራዊና ነገረ-ሰብ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ  የተዘጋጀ የጥናት ምርምር ጉባኤ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ በዛብህ በበኩላቸዉ ዩኒቨርሲቲዉ ከተመሰረተ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ለጥናትና ምርምር ልዩ ትኩረት በመስጠት ተቋሙ በጥናትና ምርምሩ ዘርፍ የተሰጠዉን ተልዕኮ በማሳካት የዘንድሮው ለአስራ አንደኛ ጊዜ የተካሄደ የምርምር ጉባኤ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት  ፕሮፈሰር አለማየሁ ቢሻዉ በቁልፍ ንግግራቸዉ  “ጥበበኛ እና አርበኛ” የሆኑ ዜጎችን ማፍራት አለብን የሚል  መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በሌላ በኩል የማህበራዊና ነገረ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ሊጠና ይገባል በሚል ርዕስ በማነቃቂያ ንግግራቸዉ “ለእዉነት መፍራት አያስፈልገንም” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በጉባኤዉ መርሃ-ግብር የአማርኛ ቋንቋ ሰዋሰዉ ግንዛቤና አተገባበር፣ የሆቴል ዘርፍ ያለዉን ስነ-ምግባር፣ ዘርን መሰረት ያደረገ ግጭት በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ስላለዉ ሁኔታ፣ የስነ ጹሁፍ ለሰላምና ለግጭት ያለዉ ሚና፣ ዲሞክራሲና ሰላም ከ2018 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለባቸዉን ፈተናዎች፣ የመሬት አጠቀቃም በላይኛዉ የአባይ ተፋሰስ አገሮች፣ የመሬት መራቆት፣ የተቃርኖ ፖለቲካ ከ2018 በኋላ በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመሬት ወረራዎችና በነዋሪዎች ላይ ያመጣዉ ተጽኖ በሚሉ ርዕሶች ላይ ትኩረታቸዉን ያደረጉ ጥናትን መሰረት ያደረጉ ጹሁፎች ቀርበዋል፡፡  

በጉባኤዉ ማጠቃለያ አዲስ ሀሳብ መፍጠር መልካም ስብዕናን መገንባትና ማህበረሰብ በመለወጥ የሀገርን አንድነት ማስቀጠል የሚቻለዉ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናትና ምርምር ከማድረግ ባለፈ በስነ-ምግባራቸዉና በክህሎታቸዉ የላቁ ወጣቶችን ካፈሩ ብቻ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

Print Friendly, PDF & Email

Photo Gallery

DMU Radio Broadcasting . . .