ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቡሬ ካምፓስ ሁለተኛውን አመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በደማቅ ሁኔታ አካሄደ

  • -

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቡሬ ካምፓስ ሁለተኛውን አመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በደማቅ ሁኔታ አካሄደ

 

ደ/ማ/ዩ፡-ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቡሬ ካምፓስ ሁለተኛውን አመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ “የተቀናጀ የእሴት ሰንሰለት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል ጥሪ የተደረገላቸው እንግደች፣ ተመራማሪዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣የአካባቢው ነዋሪዎችና የካምፓሱ ማህበረሰብ በተገኙበት በቡሬ ካምፓስ ከግንቦት 14-15/2013 ዓ.ም  በደማቅ ሁኔታ አካሂዷል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ሲስተር ገነት ደጉ በጉባኤው መክፈቻ ንግግራቸዉ ደብረ ማርቆስ የኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ላይ የትኩረት አቅጣጫውን አድርጎ ለአካባቢው ማህበረሰብ ችግር ፈች የሆኑ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ለማህበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

               የጉባኤዉ ከፊል ገጽታ

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የቡሬ ካምፓስ ዲን ዶክተር ጸበሉ አባይነህ በበኩላቸው በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው በ2006 ዓ/ም ካምፓሱ በመደበኛው የመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ-ግብር በአራት የትምህርት መስኮች 175 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ካምፓሱ አንድ ዲን፣ አምስት ምክትል ዲኖች፣ አሰራ አራት ኦፊሰሮች እና አስራ ሁለት ትምህርት ክፍሎች እንዳሉት ገልጸው ካምፓሱ የተጠናቀቁና በመሰራት ላይ ያሉ የማስፋፊያ ግንባታዎችን በመጨረስ በቀጣይ የቅበላ አቅሙን የበለጠ በማሳደግ የመማር-ማስተማር ሂደቱን ለማሳለጥ  እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጉባኤው  ቁልፍ ንግግር አድራጊ በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አበባው ጋሻው በንግግራቸዉ “የአንድ ሀገርን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ በእዉቀት ላይ የተመሰረተ ጥናትና ምርምር ላይ ትኩረት አድረጎ መሰራት አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡

ለሁለት ቀናት የቆየው የምርምር ጉባኤ በሶስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን እነሱም ግብርና ተፈጥሮ ሃብት፤ ስነ-ምግባር፣ ሰላምና ፆታዊ ተሳትፎ  እና ቢዝነስና ኢኮኖሚ ሲሆኑ በአጠቃላይ 28 ጥናትና ምርምር ስራዎች በአጥኝዎች ቀርበው ተሳታፊዎች ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ሰጥተውባቸዋል፡፡ ከእዚህ ጋር ተያይዞ በአውደ ጥናቱ የቀረቡት የጥናትና ምርምር ስራዎች ከወረቀትነት አልፈው ወደ መሬት ወርደው የማህበረሰቡን ችግር ፈች ሊሆኑ ይገባል ተብሏል፡፡

በመጨረሻም በቡሬ ከተማ የተገነባው ፌቪላ የምግብ ዘይት ማምረቻ ኮምፕሌክስ ፋብሪካና  በካምፓሱ የተጠናቀቁና በመሰራት ላይ ያሉ የማስፋፊያ ግንባታዎች ጉብኝት ከተካሄደ በኋላ ለጥናትና ምርምር አቅራቢዎችና ለክብር እንግዶች የእዉቅናና የምስጋና የምስከር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

Print Friendly, PDF & Email

DMU Radio Broadcasting . . .