
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሐዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ ለህትመት የበቁ ስነ-ጽሑፎችን ማስመረቅ ሲሆን በዚህም መሰረት አዲስ አበባ አኰቴት ማተሚያ ቤት መስከረም 2ዐዐ8 ዓ.ም. የታተመውን “ነፍስ ይማር” የተሰኘ መፅሐፍ አስመረቀ፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር በለጠ ያቆብ በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የሚጻፉ መጽሐፎችን ለምረቃ ማቅረብ እያንዳንዱን ሰው ማስተማር ነው፣ ይህ ማለት ደግሞ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ አንድ አንድ መጽሐፍ አለ፣ በመሆኑም ቤተ እምነቶች የስልጣኔ ማመንጫዎች መሆናቸውን ተረድተው በአብዛኛው ዩኒቨርሲቲዎች የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡፡፡ ደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር የሆኑት አቶ ምንዋጋው ተመስገን መጽሐፉ በከፊል ከተተረጐመበት ጥንታዊ የብራና ላይ ጽሑፍ፣ መጽሐፉን ለማዘጋጀት አነሳሽ ምክንያት፣ የመጽሐፉ አጠቃላይ ጭብጥ እና ዋና ዋና ርዕሶችና አጫጭር ገለጻዎቻቸውን፣ ሞት ማን ነው፣ የሞት ድንግተኛነት፣ አሰፈሪነትና ስለመዘጋጀት የመሳሰሉትን በዝርዝር በወፍ በረረ ቅኝት ከገለጹ በኋላ ለሙታን ከቤት እስከ ቤተክርስቲያን የሚፈጽሙ አገልግሎቶች በትክክል ስርዓቱን ተከትሎ የሚደረጉ ትንታኔዎችንም በማቅረብ ይህን መጽሐፍ ማንበብ- ከሙስና ነፃ የሆነ ስራ መስራትንና የሰው ልጅ ከተለያዩ ተንኮሎች ወጥቶ ጥሩ ነገሮችን በማሰብና በመተግበር ሀገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንደሚቻል አቅርበዋል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አማርኛ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት የመፅሀፉ ደራሲ አባ በአማን ግሩም “ነፍስ ይማር” መጽሐፍ ለመጻፍ 3 ዓመት እንደፈጀባቸውና መጽሐፉን ለማሣተም የገጠማቸው ውጣ ውረድ ከባድ እንደነበርና ይህን መጽሐፍ ማንበብ ሰዎችን ከተንኮል ወደ ጥሩ ነገር እንደሚመራቸዉ አክለዉ አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር በለጠ ያዕቆብ ዛሬ ልዩ ቀን ነው ምክንያቱም ግዕዝ ሞቷል ለሚሉ አካላት ራሣቸው የሞቱ መሆናቸውን ያሳየ ጥናት ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ፍልስፍናዎች አሁንም ተደብቀው ያሉ በመሆኑ የጥበቡ አካል ሆነው መቀጠል ያለባቸዉ መሆኑን ከገለጹ በኋላ ትግረኛ፣ ኦሮሞኛ እና ግዕዝ ቋንቋን ዩኒቨርስቲያችን ተግባራዊ ለማድረግ የየበኩላቸዉን አስተዋጽኦ መወጣት እንዳለባቸዉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
