
ደ/ማ/ዩ፡- የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም አምስተኛውን ሀገራዊ አውደ ጥናት “ባህል ለአንድነትና ለአብሮነት” በሚል መሪ ቃል ከሚያዝያ 28-29/2ዐዐ9 ዓ.ም. በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በድምቀት አከበረ፡፡ በበዓሉ ዕለትም የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወ/ማሪያምንና ዶ/ር ሙሴ ያእቆብ የኢትዮጵያ የደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ታላላቅ የሀገሪቱ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ምሁራን፣ ደራሲያን፣ የመንግስት አመራሮች፣ የኪነ-ጥበብ አፍቃሪዎች፣ በደብረ ማርቆስ ከተማ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች የመጡ ሰራተኞች፣ ተማሪዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት በጐጃም የባህል የመዚቃ ቡድንና በአርቲስት ዮሐንስ አፈወርቅ የዋሽንት ጥዑመ ዜማ አድማቂነት በልዩ ሁኔታ ተከበረ፡፡
ሲስተር ገነት ደጉ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ሲያስተላልፉ እንደተናገሩት የኪነ-ጥበብ ሀብቶች በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ተለይተው በአግባቡ እንዲጠኑ እንዲለዩና እንዲጠበቁ ለመጭው ትውልድም በስርዓት እንዲተላለፍ ለማድረግና የባህል ልማትና ለኢኮኖሚ፣ ለማህበራዊና ለሠብዓዊ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው በማመን በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በታላቁ የኢትዮጵያ የስነ-ጽሁፍ አባት በመባል በሚታወቁት ደራሲ፣ አርበኛ፣ ገጣሚ፣ ዲፕሎማት፣ መምህርና መራሄ መንግስት በክቡር ዶ/ር ሐዲስ ዓለማየሁ ስም የባህል ጥናት ተቋም በ2ዐዐ4 ዓ.ም. እደተቋቋመ ገለፀዋል፡፡ የባህሉ ጥናት ተቋሙ ሲቋቋም ዓላማ አድርጐ የተነሳው በአካባቢው የሚገኙትን እምቅ የቱባ ባህል፣ የቋንቋ፣ የኪነ-ጥበብ እና ሌሎች ባህላዊ ሃብቶችን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሆነ በመግለጽ የባህል ጥናት ተቋሙም በውስጡ የባህል፣ የሙዚቃ፣ የስነ-ጽሁፍ፣ የግዕዝ ቋንቋ፣ የትያትር እንዲሁም ቤተ-መዛግብት ዘርፎችን በመዘርጋት ባህላቸውን፣ ወጋቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉና የሀገራቸውን ባህል ከውጭ ወረራ ለማዳን በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው የሚገኙ ምሁራን ተሰጥኦቸውንና ዝንባሌያቸውን ተጠቅመው ለተቋሙ በሚያደርጉት ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ ህዝባቸውንና ሀገራቸውን ወደ ላቀ የስልጣኔ ደረጃ ለማምጣትና በህዝቦች መካከል የባህል ልውውጥን ለማዳበር “ባህል ለአንድነትና ለአብሮነት” በሚል መሪቃል አምስተኛው ዓመታዊ አውደ ጥናት እየተከበረ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንደገለፁት ባህል ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሰብአዊ የሆነ የአንድ ማህበረሰብ የማንነትና የልማት መገለጫ መሣሪያ መሆኑን በመግለጽ አካባቢው የብዙ ብርቅየ የሆኑ ጥንታዊ የብራና መጽሐፍት፣ ስዕሎችና የእደጥበብ ውጤቶችን በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ስር በተቋቋመው በክቡር ሀዲስ ዓለማየሁ የባህል ተቋም አማካኝነት ሲቻል መሠብሠብና መሠነድ ሳይቻል ማጥናትና መለየት፣ ማስተዋወቅ እንዲሁም ለተለያዩ የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማህበረሰብ ማድረስ ሌላው ተቋሙ በሙዚቃ፣ በተውኔት፣ በኪነ-ጥበብ፣ በቅርፃቅርፆች፣ በስነ-ጽሁፍ፣ በግዕዝና በቤተ መዘክር እና ሌሎች ተግባራት በተጨማሪ የሚያከናውናቸው አብይ ተልዕኮዎች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
ዶ/ሩ በንግግራቸው አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ለባህል ልማትና ለኪነ-ጥበብ ዕድገት ትኩረት በመስጠት በክቡር ዶ/ር ሃዲስ አለማየሁ ስም ባቋቋመው የባህል ጥናት ተቋም በአካባቢው የሚገኙና የኪነ-ጥበብ ችሎታ ያላቸው ሰዎች፣ ተማሪዎችና ሌሎች ማህበረሰቦች ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም በየዓመቱ የግጥም መድብሎችን በሙያው ላቅ ያለ ዕውቀት ባላቸው ባለሙያዎች በማስገምገም እንዲታተሙ፣ ተማሪዎችም ክፍሉ በሚያዘጋጀው የስነ-ጽሁፍ መድረክ እንዲሳተፉ እያደረገ እንደሚገኝና የግዕዝ ቋንቋ ትምህርትም ለግቢውና ለአካባቢው ማህበረሰብ እየተሠጠ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የባህል ጥናት ተቋሙ አመታዊ የባህል ጥናት በማካሄድ ግጥሞች፣ ባህል ላይ ያተኮሩ ምርምሮች፣ ተውኔቶች፣ ቅኔዎች የሚቀርቡበት የባህል ጥናት ተቋም ስለሆነ ከሚያዝያ 28-29/2ዐዐ9 ዓ.ም. “ባህል ለአንድነትና ለአብሮነት” በሚል መሪ ቃል ሲያከብርም የሀገራችንን ልዩ ትውፊት፣ አብሮ መኖርን፣ መደጋገፍንና መከባበራችንን የሚያሳይ የባህላችንና የኩራታችን መገለጫ መሆን አለበት በማለት አምስተኛው የባህል አውደ ጥናት በምናከብራቸውና በምንወዳቸው የባህል ተቋምም በተሠየመላቸው ክቡር ዶ/ር ሐዲስ ዓለማየሁ ሀውልት የሚመረቅበትና የእርሳቸውን “መልዕክት ለወላጆች” የሚለውን የግጥም ስብስቦች በወራሾቹ ከዶ/ር ጽጌረዳ አበበና ከአቶ ግርማ አስፋው በዶ/ር ታየ አሠፋ አርትኦት ተሠርቶና ታትሞ የሚቀርብበት በመሆኑ በአይነቱ እስካሁን ካከበርናቸው የባህል አውደ ጥናቶች ልዩ እንደሚያደርገው ገልፀዋል፡፡
ክብርት ዶ/ር ሂሩት ወ/ማሪያም የኢፌዲሪ መንግስት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስተር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለፁት ባህል ህዝቦች በአብሮነት ሲኖሩ የሚፈጥሩት ትልቅ የመግባቢያ መሣሪያ እንደሆነ በመግለጽ ሀገራኝ ኢትዮጵያ ለዘመናት በመከባበር እና በመቻቻል ብዙ ቋንቋዎች፣ ዘርና ሃይማኖቶች፣ ከለሮችን በአብሮነት ባህል ያኖረች እንግዳ ተቀባይ ሀገር ስለሆነች እነዚህ ባህሎች በጥናትና ምርምር ተደግፈው ይበልጥ ተስፋፍተውና ጐልተው ለተከታይ ትውልድ መድረስ ይገባቸው ብለዋል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የኢፌዴሪ የባህል ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በባህል ዙሪያ በቅርበት እየሠራና በቀጣይም እንደሚሠራ በመግለጽ ለሚያስፈልጉ ማነኛውም ድጋፎችም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ የክቡር እንግዳዋ አክለው ገልፀዋል፡፡ ይህ ዓይነት የምክክር አውደ ጥናትም ባህልን ለመጠበቅና ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ስለሚጠቅም ዩኒቨርሲቲዎች በንቃት ሊሠሩበትና የሚመለከተው አካል ሁሉ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ባህሎቻችን ለዘመናት ህዝቦች አብረው ለመኖራቸው ምክንያት ለአንድነታቸውና ለአብሮነታቸው ጉልበት ለእድገታቸውም ተስፋ በመሆናቸው አክብረውና ጠብቀው ሊይዙት እንደሚገባ ለተሳታፊዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በአንኳር ንግግራቸው እንደተናገሩ መሠረታዊ የሆነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦችና ሰብዓዊ ለውጦች የሚመጡት ባህልን በማክበር፣ በመጠበቅ፣ በማሳደግ ስለሆነ እያንዳንዳችን ህብረተሠቡን፣ አካባቢዉን፣ ወጉንና ባህሉን ተኮር ያደረገ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ መመሪያ፣ ደንቦች ስራዎች የህዝቡን ባህል ያጤኑ መሆን እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡
በአምስተኛው የሐዲስ ዓለማየሁ አመታዊ የባህል አውደ ጥናት ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ያሠራው የክቡር ዶ/ር ሐዲስ ዓለማየሁ ሀውልት በዩኒቨርሲቲውና በፌደራል ከፍተኛ አመራሮች፣ ከሀገሪቱ በመጡ የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች፣ በምስ/ጐጃም ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የከተማው ማህበረሰቦችና ተማሪዎች በተገኙበት በድምቀት ተመርቋል፡፡

አቶ ግዛቸው አንዳርጌ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የክቡር ዶ/ር ሐዲስ ዓለማየሁ ሐውልትን እንዲያስመርቁ ዶ/ር ሂሩት ወ/ማሪያም የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ የምስ/ጐጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ አቶ አማረ አለሙ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባን በመጋበዝ እንግዶች በአንድነት ሐውልቱን መርቀው ለህዝብ እይታ ይፋ አድርገዋል፤ ንግግርም አካሂደዋል፡፡
አውደ ጥናቱ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሁፎችና የኪነ-ጥበብ ስራዎች የቀረበ ሲሆን አቶ ግዛቸው አንዳርጌ የተቋሙን አጠቃላይ አንቅስቃሴ የሚቃኝ አጭር ሪፖርት አቅርበው በውይይትና በጥያቄ የቀጣይ ተግባራት የትኩረት አቅጣጫዎች ከምሁራን ጋር በጋራ ተጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ሲስተር ገነት ደጉ ዩኒቨርሲቲው የተሠጡትን ጠቅላላ አስተያየቶች ገንቢና ትልቅ ሚና ስላላቸው ወደ ተግባር እንደሚቀይሯቸው ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ለአውደጥናቱ ዝግጅት የጐላ ተሳትፎ ለነበራቸው ሙህራን፣ አመራሮች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎች የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች የሽልማት ስነ-ስርዓት የተበረከተ ሲሆን የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ስር የሚገኘውን ቤተ-መዛግብት (Archive Centre) በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ክፍል መምህር እና የቤተ-መዘክሩ ኦፊሰር በሆኑት በአቶ ሰለሞን አሻግሬ አስጐብኝነት ጉብኝት አድርገው፣ ጥያቄዎችን አንስተው፣ ውይይት ከተደረጉባቸው በኋላ የአውደጥናቱ ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡
