
ደ/ማ/ዩ፡- በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በባዮሎጂ ትምህርት ክፍል የተደራጁ የዱር እንስሳት ቅርስ መዘክር የዩኒቨርሲቲው የተለያዩ አካላት በተገኙበት ግንቦት ዐ3/2ዐዐ9 ዓ.ም. ጉብኝት ተደረገ፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን የሆኑት አቶ ይልቃል በዜ የመዘክሩን ጉብኝት በንግግር ሲከፍቱ እንደገለፁት የሌሎች ምሁራን ሀሳብና መረዳዳት ቢኖርም ሃሳቡን ያመጣውና ስራውን በአብዛኛው የሰራው ዶ/ር መሰለ ይሁኔ እንደሆነና ሙዚየሙን የተሟላ ለማድረግ በቀጣይ በነፍሳት፣ በትናንሽ እንስሳትና በመሳሰሉት እንደሚሰሩ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በ2ዐዐ8 ዓ.ም. ከፍተኛ የሆነ ነውጥ በነበረበት ሰዓት ለስራ ያላቸውን ፍላጐትና ተነሳሽነት ሰንቀው በመያዝ የተለያዩ ቅርሶችን እየሰበሰቡ እንዳመጡና በ2ዐዐ9 ዓ.ም. የተወሰኑትን እንዳመጡ አክለው ገልፀዋል፡፡
ይህ ሙዚየም ለተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ተማሪዎች፣ ለግብርና ተማሪዎች እንዲሁም ለሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የዱር እንስሳት ተፈጥሮ ቅርስ መዘክር በ2ዐዐ9 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተቋቋመ ሲሆን አላማዎቹም፡- ለመጀመሪያና ለ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች የተግባር ትምህርት ማስተማሪያና መመራመሪያ እንዲሆን፤ በዩኒቨርሲቲው አካባቢ ለሚገኙ የተለያዩ አካላት ስለ ዱር እንስሳት ጥቅምና እየደረሰባቸው ስላለው ጫና ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲረዳ እና ቤተ-መዘክሩን ለጐብኝዎች ክፍት በማድረግ ለዩኒቨርሲቲው የገቢ ምንጭ ማድረግ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በቤተ-መዘክሩ ውስጥ አጥቢዎች፣ አእዋፍ፣ አሳዎች እንዲሁም ተሳቢና ተራማጅ እንስሳትን የሚወክሉ ቅሪት አካላት ይገኛሉ፡፡ መዘክሩን በተሻለ መልኩ ለማደራጀት በቀጣይ ከዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ግምጃ ቤት ተጨማሪ ቅርሶችን መሰብሰብ እና በክልል ከሚተዳደሩ ፓርኮች እና በዘርፉ ከሚሰሩ ሌሎች ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ቅርሶችን ማሰባሰብ ሲሆን ሌላው ተግባር ደግሞ የቅርሶቹ ንጽህና እንዲጠበቅ ከንክኪ ነፃ እንዲሆኑ ለማድረግ የመስታወት መደርደሪያዎችን በመስራት ማስቀመጥ እና በቅርሶች አቀማመጥና አያያዝ ዙሪያ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዱር እንስሳት ተፈጥሮ ቅርስ መዘክር እንዲሁም ከታክሲደርሚ ስራ አምራቾች ህብረት ሥራ ማህበር ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግና ባለሙያዎችን በመጋበዝ ስልጠና መውሰድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መዘክሩን ለጐብኝዎች ክፍት ማድረግና በአካባቢው ለሚገኙ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራን የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት እንደሆነ ዶ/ር መሰለ ይሁኔ ገልፀዋል፡፡ ከገለፃው በመቀጠልም ዶ/ር መሰለ “የዱር እንስሳት ሀብቶቻችንን እንወቃቸው“ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም በጐብኝዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ከተሰጠባቸው በኋላ መዘክሩ ጥሩ የሆነ ጅማሮ እንዳለው እና ለመዘክሩ የሚሆን ራሱን የቻለ ቦታ መኖር እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር ጌታነህ በላቸው በበኩላቸው ከተለያዩ ቦታዎች ከ5ዐዐ ያላነሱ እጽዋት እንደተሰበሰቡና በግቢ ውስጥ ያሉ እጽዋትም ጊዜያዊ በሆነ ወረቀት ስያሜ እንደተሰጣቸው በመግለጽ ቀጣይ ለሚሰሯቸው ስራዎችም በየደረጃው ያሉ አካላት ለሚጠየቀው ጥያቄና ድጋፍ ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
