ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠና ቸውን የህክምና ዶክተሮችን በደመቀ ሁኔታ አስመረቀ

ደ/ማ/ዩ፡- በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ት/ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የህክምና ዶክተሮችን በኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ጥላዬ ጌቴን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራል የትምህርት አመራሮች፣ የአማራ ክልል የጤና ቢሮ ም/ኃላፊ፣ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛና በየደረጃው የተቀመጡ አመራሮች፣ መምህራንና ሰራተኞች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሠቦች በተገኙበት ሚያዝያ 21/ዐ8/2ዐዐ9 ዓ.ም. በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ አዳራሽ በድምቀት አስመረቀ፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ የምረቃ ስነ-ስርዓቱን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገትና ብልጽግና ቁልፍ መሣሪያ በመሆኑ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት የግልና የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በማስፋፋት ሃገራችን ኢትዮጵያ በተለይ በጤናው ዘርፍ በሠጠችው ልዩ ትኩረት የጤና ባለሙያዎችን እጥረትና የጥራት ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችን ተቀብሎ እያሠለጠነ እንደሚገኝ በመግለጽ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲም በዘርፉ በ2ዐዐ4 ዓ.ም. 72 ተማሪዎችን በአዲሱ የህክምና ትምህርት ዘርፍ (New Innovation Medical Education) ተቀብሎ ሲያሰለጥን ቆይቶ ሚያዝያ 21/ዐ8/2ዐዐ9 ዓ.ም. 44 የመጀመሪያ የህክምና ዶክተሮች ማስመረቁን ገልፀዋል፡፡

ዶክተሩ በንግግራቸው አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው የራሱ ማስተማሪያ ሆስፒታል ሳይኖረው በአስቸጋሪና በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ከደብረ ማርቆስ ሆስፒታል ጋር በትብብርና በጋራ ስምምነት በመስራትና ከጤና ጥበቃ ሚኒስተር የቅርብ ድጋፍ በማግኘት በተለየ መንገድ የችግሮችን መፍትሔ ለማፈላለግ የትምህርቱ ዋና ተዋናይና ባለቤት የሆኑት ተመራቂ ተማሪዎች በጉጉት ሲጠብቁት ለነበረው ለምረቃ ቀናቸው መብቃታቸውን በደስታ ገልፀው ከመማር ማስተማሩ ባሻገር ዩኒቨርሲቲው ሲኒየርና ጠቅላላ ሃኪሞችን በደብረ ማርቆስ ሆስፒታል በየዘርፋቸው በማገልገል የነበረውን የህክምና ባለሙያ እጥረትን በመቅረፍ ለህብረተሰቡ ላደረጉት ቅንና አኩሪ ተግባራቸው በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለህክምና ት/ቤት የህክምና ባለመያዎች ልባዊ ምስጋናቸውን ቸረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የተሻለ ተግባር ተኮር ትምህርት ለመስጠትና ለማህበረሰቡ የተሻለ የጤና አገልግሎት የሚሠጥ የማስተማሪያ ሆስፒታል በመገንባት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርትና አገልግሎት እንደሚሠጥ አክለው ገልፀው በመጨረሻው የህክምና ዶክተሮች የተማሩት ትምህርት የሠውን ልጅ ጤናና ደህንነት የሚፈውሡበት አኩሪ ሙያ በመሆኑ በሙያቸው ያስተማራቸውን ህዝብና መንግስት በቅንነት፣ በታማኝነት፣ ሙያዊ ስነ-ምግብራቸውን ተላብሠው ለማገልገል በምረቃት ቀናቸው በደረሡበት የትምህርት እርከን ላይ የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ሳይሠለቹ መስራት እንዳለባቸው በጥብቅ አደራ አሳስበዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ እይላቸው ጌታቸው በበኩላ   ቸው የአንድ ሃገር የልማትና እድገት የሚወሠነው ዜጐች ለትምህርት በሚሠጡት ግምት ያህል በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው ሠላማዊ የመማር ማስተማር ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ተገቢውን እውቀትና ክህሎት በመቅሠም በስነ-ምገባር ታንፀው በመውጣት ሀገራቸውን ከድህነትና ኋላ ቀርነት በማላቀቅ በቁርጠኝነትና በጽናት ለመወጣት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡ ለተመራቂ ዶክተሮችም በምረቃ ቀን የለበሱት ካባ መመረቃቸውን ብቻ የሚያበስር ሳይሆን ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ለሀገራቸው የእድገት ሥኬት በቁርጠኝነት የሚሠሩበት የቃል ኪዳን ካባ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በመቀጠልም በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ት/ቤት ዲን ዶ/ር የኔሰው ታምር ተመራቂ ተማሪዎች በይፋ መመረቃቸውን በማብሠር የቃለ-መሃላ ስነ-ስርዓት አካሂደዋል፡፡ በመቀጠልም ከት/ቤቱ 1ኛ ለወጣው ተማሪ የመዳሊያ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

በመጨረሻም ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ በመዝጊያ ንግግራቸው ለተመራቂ ዶክተሮች የስራ መመሪያ ሲሠጡ እንደተናገሩት ተመራቂዎች በምረቃ ቀናቸው የተቀበሉት ኃላፊነት የሠውን ልጅ በአስቸጋሪ ሁኔታ ጊዜ የሚታደግ በመሆኑ ኃላፊነታቸው የሙያ፣ የግዴታና የሰብዓዊነት እንደሆነ በመገንዘብ ጊዜያቸውን ሙያቸውና የስራ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት በተመደቡበት ቦታ የህዝባችንን ጤንነት በመጠበቅ ጤናማና አምራች ዜጋ መፍጠር እንደሚገባቸው በአጽኖት በማሳሰብ የምረቃት ሥነ-ስርዓቱ ተጠናቋል፡፡