
ደ/ማ/ዩ፡- በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም “አንፃር በእንቅልፍና እድሜ ልብ ወለድ” በሚል ርዕስ ላይ በ19/ዐ8/ዐ9 ዓ.ም. የሥነ-ጽሑፍ ሂስ መድረክ አካሄደ፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ መምህር የሆኑት አቶ ይኸነው መለሰ የስነ-ጽሁፍ ሂስ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት ሂስ ማለት ተንትኖ ማንበብ/ ትንታኔና ምክንያት ያለው ንባብ/ ማለት እንደሆነ ለቋንቋ ሰዎች፣ ምሁራንና ተማሪዎች አንድን ጽሁፍ ሂስ ማድረግ በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ እንደሆነ እና ሂስና ማህበረሰብ የሚሉ ሁለቱ ቃላቶችም ተያያዥነት ያላቸው እንደሆኑም ገልፀዋል፡፡ በዕውቀቱ ስዩም አጭር ልብ ወለድ፣ ረጅም ልብወለድ፣ ኢ-ልብወለድ እና ሌሎችንም የፃፈ ደራሲ እንደሆነ እና ለቀጣይም በልብ ወለድ ውስጥ ያለው ርዕስ፣ ወቅቱ፣ ቅርፁና ይዘቱ የሚያነጋግር እንደሆነ መምህሩ አክለው ገልፀዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ መምህር የሆኑት አቶ ሽፈራው እጅጉ በበኩላቸው የሥነ-ጽሁሐፍ የሂስ መነሻ ጽሁፉን ከበዕውቀቱ ስዩም ከ2ዐዐ7 እትም ላይ የወሰደ መሆኑንና ስለ በዕውቀቱ ስዩም ሥራዎችም የተወሰኑትን ለመግለጽ ችለዋል፡፡
የስነ-ጽሁፍ ሂስ መድረኩ አላማም ልብወለድ እንዲነበብ መቀስቀስ እና በልብ ወለድ ውስጥ አንፃር እንዴት እንደቀረበ ማሳየት መሆኑም ተገልጿል፡፡
የቀረበው ልብ ወለድም የሶስት አጫጭር ልብ ወለዶች ስብስብ እንደሆነና የተለያዩ ሶስት ንዑስ ርዕሶች /መቅረብና መራቅ፣ ማየትና መጋረድ እና መውጣትና መውረድ /እንዳሉት፣ በልብ ወለዱ ውስጥ ምን እንደሚመስሉ በስፋት በመነሻ ጽሑፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡
በሂስ መድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ መምህራን፣ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡ የእንግሊዝኛ መምህራንም ከሙያ መስካቸው አኳያ የተለያዩ ትንታኔዎችን ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም በቀረበው መነሻ ጽሑፍና ትንታኔ መሰረት የተለያዩ ሃሳቦች ላይ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው በመነሻ ጽሑፍ አቅራቢው በአቶ ሽፈራው እጅጉ እና በሥነ-ጽሁሐፍ ባለሙያው በአቶ ደርጃው አየነው ምላሽ ተሰጥቶባቸውና አንድ ልብወለድ እንደ አንባቢው እይታ እንደሚፈረጅም አስተያየት ተሰጥቶበት የሂስ መድረኩ ተጠናቋል፡፡
