
ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ
ደ/ማ/ዩ፡- በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዩኒቨርሲቲው ለ9ኛ ጊዜ የሚያካሂደውን የተማሪዎች የምረቃ ፕሮግራም አስመልክተው ፕሬዚዳንቱ እና አራቱ ምክትል ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ በመግለጫቸው ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን የመጡትን ጋዜጠኞች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው ከተመሠረተ አስር ዓመታትን ያስቆጠረው የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በ2ዐ25 በአፍሪካ 1ዐ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን ራዕይ አስቀምጦ የሰለጠነ የሠው ኃይል ማፍራት፣ ችግር ፈች ምርምር ማካሄድና ማህበረሰብ ተኮር የሆነ የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ተልዕኮውን አንግቦ ጥረት እያደረገ የሚገኝ የ2ኛው ትውልድ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በአንድ ፋኩልቲና በ8 ትምህርት ክፍሎች ስራውን የጀመረው ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ላይ 49 ቅድመ እና 3ዐ ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን በሰለጠነ የሠው ኃይልና በጥናት ላይ የተመሠረቱ ፕሮግራሞች እንደተከፈቱ በመግለጽ 30ሺ የሚደርሱ ተማሪዎችን በተገቢው ብቃትና ክህሎት አስመርቆ ወደ ስራ ያስገባ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ 5983 በ2ዐዐ9 ዓ.ም. ያስመረቃቸውና የሚያስመርቃቸው ተማሪዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ በመምህራን ልማት መርሃ ግብር የመምህራንን ብቃት ለማሳደግ በውስጥና በውጭ ሀገር በ2ኛ እና 3ኛ ድግሪ የትምህርት መስኮች ከ35ዐ በላይ መምህራን እያስተማረ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የስነ-ትምህርት ስነ-ዘዴን፣ ማስተማርን፣ ተከታታይ ምዘናን እና ሌሎችን በተመለከተ ለመምህራን አጫጭር የሙያ ስልጠና በመስጠት ውጤታማ ስራ እየተሠራ እንደሆነ ዶክተር ንጉሴ በመግለጫቸው ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ግብዓትን በተገቢው መንገድ ለማሟላት ከ91 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የሳይንስ ዘርፎችን ለማሳደግ ዕቃዎችን በመግዛት ለትምህርት ጥራት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ሁለተኛው ተልዕኮ ጥናትና ምርምር እንደሆነ በመግለጽ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ዘርፍ ከፍተኛ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህልም በጮቄ ተፋሰስ ላይ የምርምር ስራዎችን በተለይ በግብርና፣ በሰብል ልማትና ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስነ-ምህዳሩን የመጠበቅ ስራ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በባህል ጥናት በሐዲስ ዓለማየሁ ስም በተቋቋመው ክፍል በባህል ጥናት ምርምር፣ በግጭት አፈታት፣ በትምህርት፣ በማህበራዊ መስክ እና በሌሎች ጉዳዮች በርካታ ምርምሮችን እንደሚያደርጉ በመግለጫው ወቅት ተብራርቷል፡፡
ሌላው ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ማህበረሰቡን መሠረት ያደረገ የስልጠና ፍላጐት በመለየት በትምህርት፣ በፍትህ፣ በሴቶች ጐጂ ልማዶች ላይ ስልጠና ይሠጣል፡፡ በክረምትና በተለያዩ ወራት ልዩ ተሠጥኦ ያላቸው ህፃናትን በመመልመል ስልጠና ይሠጣል፡፡ በተጨማሪም በስድስት ወረዳዎችና በምስራቅ ጐጃም ዞን ስር በሚገኙ ሁለት ማረሚያ ቤቶች ነፃ የህግ ማማከር ስራ እንደሚሠራና ምርጥ ዘርን ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ከአንድ የውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ገልፀዋል፡፡ የእግር እብጠት በሽታን መከላከል ላይም ዩኒቨርሲቲው ከሚሠራቸው ስራዎች መካከል ሌላው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ከተለያዩ የብዙሃን መገናኛ ድርጅቶች የመጡ ጋዜጠኞች ጥያቄዎችን በማንሳት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ እና በአራቱ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጨምሮ ማብራርያ ተሰጥቷል፡፡
