
የቅድመ ምረቃና የማስተርስ ፕሮግራሞችን እየሠጠ የሚገኘው የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በ2011 የዶክትሬት ዲግሪ እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡ በቅድመ ምረቃና በማስተርስ ፕሮግራም የተመዘገበውን ውጤት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ዩኒቨርሲቲው የዶክትሬት ዲግሪ ይጀምራል፡፡
የ2009 ዓ.ም የተማሪዎች የምረቃ በዓልን አስመልክቶ ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ.ም በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ የትምህርት ልማትን አስመልክተው ሲናገሩ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት ያሉትን ፕሮግራሞች በማጠናከር የሶስተኛ ዲግሪ በ2011 የትምህርት ዘመን መጀመር የሚያስችለው አቋም ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች የሚጀመሩት የመምህራን ልማት በሚሟላባቸው አምስት ወይም ስድስት ትምህርት ክፍሎች ሲሆን ይህንን የሦስተኛ ዲግሪ መስጠት የሚያስችል ቁመና ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ እንዳለውም ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ አብራርተዋል፡፡
በዚህ አካሄድም የሶስተኛ ዲግሪ የሚጀመርባቸው ትምህርት ክፍሎች ከአሁኑ በትምህርት ክፍሉ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እየሰሩ በትብብር ከሚሰሩ አቻ ተቋማት ጋርም ትስስር በመፍጠር ሥርዓተ-ትምህርት ቀረፃ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡
