
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች የሰሩትን ስራ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተክለሃይማኖት ትምህርት ቤት በተዘጋጀው የኢግዚቢሽን ማዕከል ላይ አቀረቡ፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የልዩ ችሎታና ተሰጥዖ ማበልጸጊያ ማዕከል መኰነን አቶ ገበየሁ ሽፈራው እንደገለፁት ማዕከሉ ከተቋቋመበት ሀምሌ 1/2ዐዐ8 ዓ.ም. ጀምሮ ለተማሪዎች የማማከር፣ የድጋፍና ክትትል አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን ዋና አላማውም ልዩ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡
እንደ መኰነኑ ገለጻ ልዩ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች የማወዳዳሪያ መስፈርት በማዘጋጀት የሚመለመሉ ሲሆን መስፈርቱም እንደየትምህርት መስኮች ባህሪ የተለያየ ነው፡፡ በሣይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራና የማላመድ ስራ ለመመልመል ኦርጅናል ወይም በአካባቢያችን ከዚህ በፊት ያልተሰራ፣ በአካባቢያችን ከሚገኝና በቀላል ወጭ መሰራት የሚችሉ፣ ችግር ፈች የሆነ፣ የፈጠራው ባለቤት የመግለጽ ችሎታ እና ተማሪው ለጥያቄዎች የሚሰጠው ምክንያታዊ ምላሽ እንደመስፈፈርት ተቀምጠዋል፡፡ በስነ-ጽሁፍ ዘርፍ ደግሞ ለጥያቄዎች የሚሰጠው ምክንያታዊ ምላሽ ማቅረብያ ዘዴና ምጣኔ፣ የቋንቋ አጠቃቀምና ውበት፣ የጽሑፍ አቀራረብ ዘዴና ምጣኔ፣ የጽሁፉ ጭብጥ፣ ቁጥብነትና ጥድፊያነት፣ የልብ ወለድ ባህሪያትን ስለማሟላት፣ ምትና ተጨባጭነት፣ ድምጽና የአነባበብ ስልት የመምረጫ መስፈርቶች ናቸው፡፡
ማዕከሉ በመስፈርቶች አማካኝነት የተቀበላቸውን ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ ለስራዎቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ግብአት በመለየት፣ በጀት በመመደብ፣ ግዥ በመፈጸም፣ የማዕከሉ መሳሪያዎች አዳራሽ በመስጠት እና የስልጠናና የማማከር አገልግሎት በመስጠት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች ከሣምንት ሁለት ቀናት ማለትም እሁድና ቅዳሜ እንዲከታተሉ ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ የማድረግ ስራ ያከናውናል፡፡
በመጨረሻም የክትትሉን ቀጣይነት ከማረጋገጥ አኳያ እነዚህን ተማሪዎች በማየት ዩኒቨርሲቲውም ሆነ ሌሎች አካላት ተሞክሮውን ወስደው ተግባራዊ በማድረግ ለሀገር ያለውን ፋይዳ ማሣደግ እንደሚገባና ዩኒቨርሲቲውም በየጊዜው ልዩ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች እየመለመለ፣ እያሰለጠነ በማበረታታትና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር የተሻለ ዜጋ ማፍራት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡
