
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መገባደጃ ላይ 20 ሺ ተማሪዎችን መቀበል የሚያስችል አቅም በመገንባት ላይ የሚገኘው የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ዘርፈ ብዙ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በዋናው ግቢ፣ በህክምናና ጤና ሳይንስ ካምፓስ እንዲሁም በቡሬ ካምፓስ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የግንባታ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ይገኛል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳይህ ካሳው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካካለኛ አመራር ህንፃዎችን እንዲጎበኝ ያደረጉ ሲሆን የህንፃዎች ግንባታ ያሉበትን ደረጃም ለመገምገም ተችሏል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ዶ/ር ሳይህ የህንፃዎችን አሰራር ሂደትና የተቋራጮችን አሰራር በተመለከተ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም የገንዘብ አጠቃቀምን በተመለከተ የጋራ የባንክ አካውንት በመጠቀም ችግሮችን ለመቅረፍ እንደተቻለም አብራርተዋል፡፡ ይህ የጋራ የባንክ አካውንት አጠቃቀምም ተቋራጮች በየጊዜው የሚፈጥሩትን ምክንያት በማስቀረት ገንዘቡ በአግባቡ ለታለመለት ሥራ ብቻ እንዲውል አስችሏል ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው እየሠሩ ካሉት በርካታ የግንባታ ተቋራጮች መካከልም ዮቴክ ኮንስትራክሽን በሥራ አፈፃፀም የተሻለ አቋም ያሳየ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም ከ 1300 በላይ ሰራተኞች በየቀኑ ሥራ ላይ እያሰለፈ ይገኛል፡፡ ሌሎች ተቋራጮችም ከነበረባቸው ከፍተኛ የሆነ ወደኋላ መቅረት አሁን ላይ ሥራቸውን በፍጥነት እያከናወኑ ይገኛል፡፡
በጉብኝቱ የተሳተፉት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ ዩኒቨርሲቲው በግንባታ ዘርፍ እያከናወናቸው ያሉት ሥራዎች ከፍተኛ ስለሆኑ ወቅታዊ የሆነ ግምገማና ክትትል ስለሚፈልጉ ሁሉም አመራር የግንባታ ሥራዎችን ሊመለከታቸው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ በግንባታ ሂደት ላይ ያሉት ህንፃዎች ጥራት በተመለከተም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በጉብኝቱ የተሳተፉ አባላትም የህንፃዎችን በጥራት መሰራት አድንቀዋል፡፡ ግንባታዎቹ በ2011 ሙሉ በሙሉ ለሥራ ዝግጁ ሆነው ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ ይሆናሉ፡፡ በጉብኝቱ ወቅት የግንባታ ሥራዎችን ቀጣይነት በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ተሰጥቶበታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የማስተማርያ ሆስፒታልና የመምህራን መኖሪያ ግንባታ ሥራዎች የዲዛይን ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
