የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ለ2ዐዐ9 ዓ.ም. ተመራቂዎች የአሉሚኒ ማህበሩን ተቀላቀሉ

ደ/ማ/ዩ፡- የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት “የምሩቃን ማህበር ምንነትና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ለተመራቂ ተማሪዎች በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሰኔ 27/2ዐዐ9 ዓ.ም. ለግማሽ ቀን የቆየ ስልጠና ተሰጠ፡፡

ስልጠናውን የሠጡት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደሳለው ጌትነት እንደተናገሩት የምሩቃን ማህበር ሲባል ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ተከታትለው ከጨረሱ በኋላ በስራ ዓለም ውስጥ በማንኛውም ክፍለ ዓለማት ሆነው ምሩቃንን ለሁለትዮሽ ዓላማና ጥቅም በአንድ ታዛ ውስጥ የሚያሰባስብ ማህበር ነው ብለዋል፡፡ ይህንንም አስመልክተው የአለማችን የአሉሚኒ ማህበር በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በኬንያና ሌሎች የአለማችን ሀገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለያየ የቁጥር ብዜት ዛሬ ላይ እንደደረሰም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

የምሩቃን ማህበር በ2ዐኛው ክፍለ ዘመን በአሜሪካ በአካል የተመረቁ ወንዶች በተበታተነ የገቢ ማስገኛ መንገድ ብቻ በመምራት እንደተጀመረ ቢታወቅም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግን በተለያዩ የዓለም ሀገራት ዘመኑ ባፈራው የቴክኖሎጅ ጥበብ ውጤት በሆነው በማህበራዊ ሚዲያና ኢንተርኔት እየታገዘ፣ ወንዶችና ሴቶች ተመራቂዎችን የያዘ፣ በራሱ የገቢ ምንጭ መተዳደር የጀመረና ኔትወርክ ፈጥሮ መንቀሳቀስ የቻለ ይልቁንም በአሁኑ ሠዓት ከፍተኛ አባላት ቁጥር ያላቸው የምሩቃን ማህበርን ማፍራት የቻለና ዘላለማዊ ትስስርን በምሩቃንና በተማሩበት ተቋም መካከል የፈጠረ እና እየፈጠረም ያለ እንደሆነ አቶ ደሳለው አክለው ገልፀዋል፡፡

በስልጠናው የምሩቃን ማህበር ምንነት፣ ለምንና ለማን ጥቅም፣ ታሪካዊ አመጣጡና ዳራው፣ የማህበሩ  ስኬት ልኬት፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች፣ የገቢ ማሰባሠቢያ የዘዴዎች፣ የመገናኛ መንገዶች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችም በስልጠናው የተዳሠሡ ርዕሠ ጉዳዮች ነበሩ፡፡

በመጨረሻም የስልጠናው አስተባባሪና በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአሉሚኒ ማኔጅመንት ባለሙያ በሆኑት በአቶ ስማቸው አየነው አማካይነት የተመራቂ ተማሪዎች መረጃና ተወካይ ተማሪዎችን በመመዝገብ ከ500 በላይ ተማሪዎች የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲተ የምሩቃን ማህበር አባል በመሆን ተመዝግበው የአባልነት ቅፅ ሞልተዋል፡፡