
ደ/ማ/ዩ፡- ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ “የመምህራን ተከታታይ የሙያ መሻሻል ለትምህርት ጥራት” በሚል ጭብጥ ከሰኔ 19-21/2ዐዐ9 ዓ.ም. ዓውደ ጥናት አካሄደ፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአካሚክ ጉዳዮቸ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ ጤናው ዓውደ ጥናቱን በንግግር ሲከፍቱ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በዋናነት ከያዛቸው ተልዕኮዎች ባሻገር በተለይ በመምህራን ሙያ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ላይ ሠፊ ተሳትፎ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥና በተለያዩ ኮሌጆች የከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራሞችን በማስተባበርና ስልጠናውንም በመስጠት መጠነ-ሠፊ ተግባራትን እየሠራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በተለይ በመምህራን ልማት መርሃ ግብር ላይ ቀደም ብሎ በክረምት መርሃ ግብር ይሠጥ የነበረውን አሁን በመደበኛና በ “PGDT” ፕሮግራሞች ተጠናክሮ ከሙያዊ ስልጠና ባሻገር ተግባራዊ የሆነ ስራም እየሠራ ይገኛል፡፡ ተማሪዎች ስልጠናውን በወሠዱ ዋና ባለድርሻ አካላት በሆኑ መምህራን እንዲታቀፉ መምህራንና ርዕሰ መምህራን ስልጠናውን በመስጠትና በማማከር /mentoring/ ሰፊ ድርሻ እንዳላቸው ተብራርቷል፡፡
ፕሮግራሙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ በመሆኑ የፕሮግራሙን ውጤታማነት እየገመገሙና ክፍተቱን እያሻሻሉ የተሻለውን አፈፃፀም እያስፋፉ የበለጠ ፕሮግራሙን ውጤታማ አድርጐ ከመሄድ አንፃር የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው አቶ ታደሰ አክለው ገልፀዋል፡፡
አቶ ታደሰ አያይዘውም የዚህ ስልጠና ዋና ዓላማ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ስለሆነ በፕሮግራሙ የተካተቱት ባለድርሻ አካላት ቀጥታ የሚመለከታቸው በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው ጠቃሚ አስተሳሰቦችን በመውሠድ በቀጣይ ለሚደረጉት የስልጠና ፕሮግራሞች የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የራሱ አስተዋጽኦ ስላለው በቆይታቸው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በየደረጃው የሚሠለጥነው እያንዳንዱ መምህር ሙያውን ማሻሻል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የ“GEQIP” አስተባባሪ አቶ ወንድይፍራው ምህረት በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከተቋቋሙት ክፍሎች አንዱ የሆነው የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትን ማሻሻያ ፕሮግራም የመምህራንን ተከታታይ ሙያ ለማሻሻል የሚያግዝ ከአምስቱ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች፣ ከ16ቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ከዞን ትምህርት ባለሙያዎች እና የስልጠናው አስተባባሪና ስልጠና ሰጭ ከሆነው ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ሰልጣኞች የስልጠናው ተሳታፊዎች እንደሆኑ በመግለጽ የመምህራን ተከታታይ የሙያ መሻሻል ለትምህርት ጥራት ሲሰጥ መምህራን የአንበሳውን ድርሻ ስለሚይዙ ችግሮችንና መልካም ተሞክሮዎችን በግልጽ መወያየት እንዳለባቸው ለተሳታፊዎች አሳስበዋል፡፡
በስልጠናውም አራት ከመምህራን ኮሌጆችና አራት ከዩኒቨርሲቲው የተመረጡ ሞዴል የተግባር ምርምሮች /Action Researches/ ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጐባቸዋል፡፡ በተጨማሪም በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ክላስተር ውስጥ ያሉት አምስቱ ኮሌጆች በከፍተኛ የዲፕሎማ ፕሮግራም /HDP/ አተገባበር ላይ የራሳቸውን መልካም ተሞክሮዎችንና እጥረቶችን በሪፖርት አቅርበው ጥልቅ ውይይት ተደርጐባቸዋል፡፡ ለዩኒቨርሲቲው አመራር አካላትም በርካታ ተጨማሪ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ተነስተው ምላሽ ተሠጥቶባቸዋል፡፡
ስልጠናውን የወሠዱት ባለሙያዎች በየትምህርት ቤታቸው ችግሮችን በመለየት፣ ግብዓቶችን ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን በማሟላት፣ ተግባራትን አቅዶ በመስራት ለትምህርት ጥራት መሻሻል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባቸው መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎች እንዲሁም ስፖንሠርም በማድረግ ከተለያዩ ኮሌጆችና ትምህርት ቤቶች በመግባት እንደ አንድ የማህበረሰብ አገልግሎት የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ በመግለጽና ለወደፊትም ከጐናቸው እንደሚሆን ለተሳታፊዎች አረጋግጧል፡፡
