
ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ከጣሊያን ሀገር በመጡ ሁለት ፕሮፌሰሮች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የባይፋርም አሠራርን ለማዘመን የሚያስችል በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ሴኔት አዳራሽ ለ3 ቀናት የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሠጠ፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የባይፋርም አሠራርን ለማዘመን የተሠጠውን ስለጠና በንግግር የከፈቱት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነትና ትብብር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሃይማኖት ዋሴ እንደገለፁት ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ይህንን መሠል በርካታ ስልጠናዎችን ሲሠጥ የቆየ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ጠቅሰው ከየካቲት15-17/2ዐዐ9 ዓ.ም. በቆየው ስልጠና የስልጠናው ተሳታፊ መምህራን ተገቢውን እውቀትና ክህሎት ለመጨበጥ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል፡፡ ስልጠናው በዋናነት ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለተፈጥሮና ኮምፕቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ እና ለግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ መምህራን የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት በአግባቡ ለመስራት እንዲችሉ በተለይም የግብርናው ዘርፍ ተፈላጊውን ክህሎትና እውቀት ለማስጨበጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
ስለሆነም ሰልጣኞች ከስልጠናው የሚያገኙትን ትምህርት በአግባቡ በመገንዘብ በቀጣይ ለሚሠሯቸው የምርምርና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ተግባራት ትልቅ ግብዓት ስለሚሆናቸው በትኩረትና በንቃት መሣተፍ እንደሚገባቸው ዶ/ር ሃይማኖት አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ዘርፉ በተለይም በግብርናው የትምህርት መስክ እጅግ ጠንካራ የሚባሉ ስራዎችን ለመስራት ከ2ዐ16 ዓ.ም. ጀምሮ ጣሊያን ሀገር ከሚገኘው ሞሊስ ዩኒቨርሲቲ ጋር ወዳጅነት በመመስረት በጥምረት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና የጮቄ የተፋሰስ ፕሮጀክት ቀጥታ ጋባዥነት በትምህርት ይዘቱ ላይ ጥልቅ የምርምር እውቀትና የተሻለ ልምድ ያላቸው ፕሮፌሰር ጁሴፔ እና ፕሮፌሰር አንድሬ የተባሉ ሁለት ፕሮፌሰሮች ከጣሊያን ሀገር በማስመጣት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የባዮፋረም አሠራርን ለማዘመን የሚያስችል ስልጠና ተሠጥቷል፡፡
የስልጠናውም ይዘት በሁለት አበይት ርዕሶች ዙሪያ የሚያጠነጥን ሆኖ የመጀመሪያው ይዘት “Statistical Methodology in Biology/ Agriculture” በፕሮፌሰር ጁሴፔ ተሰጧል፡፡ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳይ “Adaptive Management of Ecological System” የሚል ሲሆን በፕሮፌሰር አንድሪያ አማካይነት እንደተሠጠ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ የስልጠናውም መሠረታዊ ዓላማ በምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት አስፈላጊውን እውቀትና ክህሎት እንዲሁም በግብርናና ተፈጥሮ ሳይንስ ዙሪያ ሰልጣኞች ላቅ ያለ ዕውቀት እንዲኖራቸው ማስቻል መሆኑ ተገልጿል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች እንደገለፁት የተሠጠው የአቅም ማጐልበቻ ስልጠና እጅግ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ከመሆኑ ባሻገርም ከስልጠናው ብዙ ቁምነገሮችን መቅሠም እንደቻሉና የነበረባቸውንም ክፍተት ለመቅረፍ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም ይህ መሠል ስልጠና በቀጣይነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሣስበዋል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነትና ትብብር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ሃይማኖት እንደተናገሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንግበው ከተነሷቸው ዋና ዋና መሠረታዊ ተልዕኮዎች አንፃር የተለያዩ የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን መስጠት አንዱና ዋና ተግባራቸው እንደሆነ በመግለጽ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲም አንዱ በመሆኑ ይህን መሠል ስልጠና በቀጣይነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ሙሉ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡
