የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ ማህበር ደብረ ማርቆስ ቅርንጫፍ አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ

ደ/ማ/ዩ፡- በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ህዋ ሳይንስ ማህበር ደብረ ማርቆስ ቅርንጫፍ አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ “ኢትዮጵያ ሳይንሳዊ ህብረተሠብ ትሆናለች” በሚል መሪ ቃል መጋቢት 2ዐ/2ዐዐ9 ዓ.ም. አካሄደ፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምፒቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን የሆኑት  አቶ ይልቃል በዜ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት የህዋ ሳይንስ ማህበር በዓለም ሳይንስን ባህሉ ያደረገ ህብረተሠብ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ማህበር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በገለፃቸውም በሀገራችን የህዋ ሳይንስ እድገት ከዚህ ግባ የማይባል ቢሆንም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገራችን ኢትዮጵያም ቀስ በቀስ በአገር ደረጃ ማህበሩ አባላትን እያፈራና ቅርንጫፍ ማዕከላትን እያስፋፋ የመጣ ትልቅ ማህበር እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም  አዲሱን ትውልድ ከሳይንሱ ጋር ለማስተዋወቅ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ህዋ ሳይንስ ማህበር በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ክለቦችን በማቋቋም ማህበሩን ሊያሳድጉ የሚችሉ አስተሳሰቦችን በመሠንዘር የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚገባ ጨምረው አሳስበዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ ሶሳይቲ ደብረ ማርቆስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ተጠሪ የሆኑት ዶ/ር ይሁኔ ህብስቴ በሪፖርታቸው እንደገለፁት ወጣቱ ትውልድ ከፊቱ የተደቀኑትንና የሚደቀኑትን ተግዳሮቶች በአሸናፊነት በመወጣት አገሪቱን ባጭር ጊዜ ከድህነት አሮንቃ ለማላቀቅ ሳይንሳዊ አመለካከትን፣ እውቀትንና ክህሎትን ከምንጩ በመቅዳት ሳይንስና ቴክኖሎጅን የሚጠቀም ዜጋ መፍጠር እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ በሪፖርታቸው አያይዘውም ማህበሩ የነገዋን ኢትዮጵያንና ወሳኝ የሆነውን ዜጋ የሚቀረጽበት ትልቅ ማህበር በመሆኑ ሳይንሱን በትክክል በመገንዘብ በዳበረ ችሎታ የሚንቀሳቀስና ኢትዮጵያ ሳይንሳዊ ህብረተሠብ ትሆናለች ብሎ የሚያምን ትውልድ በመፍጠር ስለራሳችን በሚገባ እየተጠበብን መኖር ይኖርብናል ብለዋል፡፡ እንደ ዶክተሩ ገለፃም የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ ደብረ ማርቆስ ቅርንጫፍ የካቲት 8/2ዐዐ8 ዓ.ም. ሳይንስን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ መገንባት እና በኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጅ የሚሠጠውን ጥቅም ጥቆማ መስጠት በሚሉ ሁለት ዓላማዎች የተመሠረተ ሲሆን አላማውንም ለማሳካት ውስንነቶች ቢኖሩም በርካታ ሳይንሳዊ ምርምሮችን በዘርፉ ሲያከናውን የቆየ ማህበር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ መምህር የሆኑት ዶ/ር አረጋ ሙሉ በበኩላቸው ‘Simulation of hydrological effects of land use /land cover change on stream flow at Gilgel Abay River basin using PRMS model and satellite images’ በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበው ሠፊ ውይይት ተደርጐበታል፡፡ በውይይቱም በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው በባለሙያው በቂ ምላሾች ተሠጥተውበታል፡፡ በተጨማሪም ከደብረ ማርቆስ ከተማና አካባቢ ልዩ ተሠጥኦ ያላቸው ተማሪዎች የፈጠራ ስራቸውን ለጉባኤው አቅርበዋል፡፡

በማህበሩ በዓመቱ ጠንካራ ስራ ለሠሩ ሠራተኞች የሽልማት ወረቀት ተበርክቶ የማህበሩ ኮሚቴዎች ያልተሟሉ መሆኑን ዶ/ር ይሁኔ ገልፀው በቤቱ አንድ አባል አስመርጠዋል፡፡

በመጨረሻም አቶ ይልቃል በዜ በመዝጊያ ንግግራቸው እንደተናገሩት ሳይንሳዊ ህብረተሠብ መፍጠር የሚቻለው የሁሉም ህብረተሠብ ቀና አመለካከት፣ ተሳትፎና ሳይንሳዊ ተግባቦት ሰፍኖ ጠንካራና ሳይንስን የተከተለ አሠራር ሲኖር መሆኑን ገልፀው ሁሉም አባላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡