
ደ/ማ/ዩ፡- ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች የመንግስት ፋይናንስ ድርጅቶች ዋና ዳይሬክተር፣ ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የገንዘብና ኢክኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጥላሁን መሀሪ እና ሌሎች በየደረጃው የተቀመጡ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሠቦች በተገኙበት ሰኔ 24/2ዐዐ9 ዓ.ም. በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በድምቀት አስመረቀ፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ እይላቸው ጌታቸው የምረቃ ስነ-ስርዓቱን አስመልክተው ለተመራቂ ተማሪዎች መልዕክት ሲያስተላልፉ እንደተናገሩት ትምህርት ለአንድ ሀገር የልማትና የእድገት መሠረት በመሆኑ ስለ ትምህርት ሲታሰብ ስለ አንድ ሀገር ልማትና ብልጽግና ይታሠባል፡፡ በመሆኑም ልማት ደግሞ በዜጐች እውቀት፣ አቅምና ጉልበት የሚመጣ እንደሆነ ያደጉ ሀገራትን ታሪክ ማየት በቂ ነው፡፡ ስለሆነም ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህን በመገንዘብ ለወጣቶች የትምህርት ዕድል በመፍጠር በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያሉት ተማሪዎች ደግሞ ከግማሽ ሚሊዮን የሚያንሱ መሆናቸውን ለሃገር ልማት ተመራጭ ግብዓት እንደሆነ ተማሪ እይላቸው ገልፀዋል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ተገቢውን እውቀትና ክህሎት በመቅሠምና በስነ-ምግባር ታንፀው በመውጣት ሀገራቸውን ከድህነትና ኋላቀርነት በማላቀቅ በጽናትና በኩራት ለሐገራቸው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ተመራቂ ተማሪዎች የለበሱት ካባ ከመመረቃቸው ባሻገር እውቀታቸውን በተግባር ለሐገራቸው የእድገት ስኬት የሚያውሉበት የአደራና የቃል ኪዳን ካባ መሆኑን ተገንዝበው ተመራቂዎች በሄዱበት ቦታ ሁሉ በቅንነትና በታማኝነት ለሐገራቸው እንዲሰሩ ተማሪ ይላቸው አሳስቧል፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ በበኩላቸው በምረቃ በዓሉ ወቅት ለተመራቂ ተማሪዎች ባደረጉት ንግግር ትምህርት ለዜጐች እድገትና ብልጽግና ጉልህ ሚና ስላለው ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ለትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እንደሰራች በመግለጽ ባለፈችበት የ1 ክፍለ ዘመን የዘመናዊ ትምህርት ታሪኳ አሁን ያለንበት ዘመን ሲታይ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች እምርታዊ ለውጥ የታየበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡ ዘመናዊ ትምህርት በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ለማግኘት በጣም ጠባብና በጣት የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርት የሚያገኙበት ወቅት አልፎ ባሁኑ ሰዓት ሀገሪቱ በርካታ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎችን በሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት ተከፍተው የሚፈለገውን የሠው ኃይል በመቅረጽ ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በ1ዐ ዓመት የትምህርት ሂደት ውስጥ ከ3ዐ ሺ በላይ ተማሪዎች እያሠለጠነ የሚገኝና ባሳለፋቸው የትምህርት ዘመናትም በርካታ ተማሪዎችን አሰልጥኖ በማስመረቅ ለገበያ ያቀረበ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን በመጥቀስ በ2ዐዐ9 ዓ.ም በቅድመና ድህረ ምረቃ መስኮች በጠቅላላው 5983 ተማሪዎችን እያስመረቀ ይገኛል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው ስድስቱ ስነ-ምህዳሮች የሚገኙበትና ትልቁ የውሃ ጋን የሆነው የጮቄ ተፋሠስን የዩኒቨርሲቲው መለያ ብራንድ ለማድረግ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ በሰብል ልማት፣ በእንስሳት ልማትና በሌሎች መስኮች ችግር ፈች ጥናትና ምርምር ዩኒቨርሲቲ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ ፡፡
ዶ/ር ንጉሴ አያይዘውም የአካባቢውን ቱባ የማህበረሰብ፣ ባህል፣ ወግ፣ ቋንቋ ልማድና ስነ-ጥበብ በማጥናት ሀገር በቀል የባህል ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት በእውቁ ደራሲ፣ አርበኛና ዲፕሎማት በክቡር ዶ/ር ሃዲስ አለማየሁ ስም የባህል ጥናት ተቋም አቋቁሞ ጥናትና ምርምሮችን፣ አመታዊ አውደ ጥናቶችንና ሲምፖዚየሞችን በማድረግና በእርሳቸውም መታሠቢያ ይሆን ዘንድ የሚያምር ሃውልት በደብር ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አደባባይ አቁሞላቸዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ንጉሴ ገለጻ የማህበረሰቡን ፍላጐት ከግምት ውስጥ ያስገባ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት፣ ነፃ የህግ አገልግሎት፣ የማማከር ስራ፣ የወጣቶች የፈጠራ ስራ ድጋፍ እና መሠል ተግባራትን በመተግበር በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬድዮ ትምህርታዊና አዝናኝ ፕሮግራሞችን እያቀረበ የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ በመግለጽ ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ማጠናቀቂያ የቅበላ አቅሙን ወደ 2ዐሺ ለማድረስ በዋናው ግቢ፣ በጤና ሳይንስና በቡሬ ካምፓሶች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማውጣት ግንባታዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር ንጉሴ በመጨረሻ መልዕክታቸውም ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ላጠኑት የሙያ መስክ በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ታንፀው በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ራሳቸውን መግዛት፣ ራሳቸውን መምራት፣ ከሌሎች ወጐች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና ልማዶች ጋር እስካሁን ድረስ ብዙ አገልግሎቶች ባልተሟሉበት ችግሮችን ተቋቁመው ለመጡለት ዓላማ በስኬት መወጣት መቻላቸው ለወደፊት ህይወታቸው ጽናትና ብርታት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላም የራሳቸውንና የሐገራቸውን ህልውና የሚያስቡበት ወቅት በመሆኑ ሀገራቸውን አሁን ካለችበት የድህነትና ኋላቀርነት በማላቀቅ ወደ ብልጽግና ለማምጣት እልህ አስጨራሹን ጉዞ የሚቀላቀሉበት ሰዓት በመሆኑ ለሐገራቸው እድገት የለውጥ ሃዋርያ እንዲሆኑ ለተመራቂ ተማሪዎች አሳስበዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካዔል ለተመራቂዎች የሥራ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡ ባስተላለፉት መመሪያም ተመራቂዎች መንግስት የነደፋቸውን የልማት ፖሊሲዎችን በማስፈፀም ረገድ ከፍተኛ የሆነ ሥራ በመስራት ሃገራችን ኢትዮጵያ አነስተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ እንድትሰለፍ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ሊያደርጉ እንደሚገባ በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ስንታየሁ አያይዘውም ምሩቃን የመልካም አስተዳደር ችግርን በመቅረፍ የኪራይ ሰብሳቢነትን ዝንባሌ በመታገል ለበለፀገች ኢትዮጵያ እንዲሰሩ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመቀጠልም እጩ የመጀመሪያና የሁለተኛ ድግሪ ተመራቂዎችን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሬጅስትራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሁነኛው ደሴ አስፈፃሚነት የተለያዩ ኮሌጆች ዲኖች መመረቃቸውን አብስረዋል፡፡ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ ጤናው አቅራቢነት የክብር እንግዳው ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል እና ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ ከየኮሌጁ 1ኛ የወጡ ተማሪዎችንና በተለይ ከዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ውጤት የዋንጫ ተሸላሚ የሆኑትን ተማሪ ዘሪሁን ሽራጐ እና የሴት የዋንጫ ተሸላሚ ለሆነችው ተማሪ አሳየች አግደው የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶ የፕሮግራሙ ፍፃሜ ሆኗል፡፡
