ደ/ማ/ዩ፡- የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአቀንጭራ አረምንና አገዳ ቆርቁር ነፍሳትን ሊከላከል የሚችል የአባራሪና አጥማጅ /Push-pull/ ቴክኖሎጂን ለመተግበር አውደጥናት አካሄደ፡፡ በአውደ ጥናቱ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን ለተጠቃሚው ለማድረስም ስራ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት ረዳት ፕሮፌሰር ገነት ደጉ በእንኳን ደህና መጣችሁና መክፈቻ ንግግራቸው ሲናገሩ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከያዛቸው ተልዕኮዎች አንዱ በሆነው በምርምር ዘርፍ ጉልህና ቀዳሚ የሆኑ የህብረተሰቡ ችግሮችን በመለየት በርካታ ስራ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ በዚህም ዘርፍ በተመረጡ የምዕራብና ምስራቅ ጐጃም ዞን ወረዳዎች በተከሠተው የበቆሎን ተባይ ለመከላከል አባራሪና አጥማጅ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የተዘጋጀ ወርክሾፕ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ከበቆሎ በተጨማሪም በሌሎች ሰብሎች ላይ ሊከሠቱ የሚችሉትን ተባዮች ግብርና ጽ/ቤቶች፣ አጋር አካላት፣ አርሶ አደሮችና በቀበሌና በዞን የተሠማሩ ባለሙያዎች ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምረት በመስራት ቅድመ መከላከል ማድረግ እንዳለባቸውም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በወርክሾፑ ፅሁፍ ያቀረቡት ዶ/ር ተወልደብርሃን ገ/እግዚአብሔር የዘላቂ ልማት መካነ ጥናት አጋር አካል አውደ ጥናቱ የአፈር መከላትን የሚከላከል ወርክሾፕ እንደሆነ ገልፀው በተፈጥሮ ግብርና ላይ ያተኮረ ስርዓተ-ምህድራዊ የተፈጥሮ ግብርናን ማሻሻል የሚያስችል ከተፈጥሮ ጋር የሚስማማ ግብርና፣ የአፈር ምርታማነትን የሚጨምር የግብርና ስርዓት፣ ምርታማነትን የሚጨምር አሰራር መሆኑን አስረድተልዋል፡፡ ይህም ሲሆን የአፈር ንጥረ ነገሮች ተጠርገው እንዳይሄዱ እንደየአካባቢው ሁኔታ በማጥናት ዘልማዳዊ የሆነውን የግብርና ስርዓት መቀየርም አንዱ የወርክሾፕ ዓላማ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ሱ እድዋርድስ /Sue Edwards/ የዘላቂ ልማት መካነ-ጥናት አጋር አካልና የዶ/ር ተወልደብርሃን ገ/እዚአብሔር ባለቤት በወርክሾፑ ግብርና የተወሳሰበ ስርዓት ያለው ግን አስፈላጊ የሆነ የተፈጥሮ ግብርና ምርቶችን መጨመር የሚያስችል ዘዴን ሊቃኝ የሚችል ፕሮጀክት በመሆኑ መሬታችንን በአግባቡ በመጠበቅ ለአካባቢ ሙቀት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት የጥንት አያቶቻችንን ታሪክ ልንመለስ ይገባል በማለት ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር መስፍን አባተ እና ዶ/ር ብርሃኑ ዓለሙ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቱ አባል ሲሆኑ ከንድፈ ሐሳብ ቅበላው እስከ አተገባበሩ ያለውን የአባራሪና አጥማጅ ቴክኖሎጅ አሠራርን በሰፊው አቅርበዋል፡፡ በገለፃቸውም በቆሎ በምዕራብና ምስራቅ ጐጃም ዞኖች በስፋት የሚመረት ምርት ቢሆንም አገዳ ቆርቁርና አቀንጭራ የአፈሩን ለምነት በመቀነስና በቆሎውን በቀጥታ በማጥቃት ምርታማነትን እየቀነሡት መጥተዋል፡፡ ይሁን እንጅ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና አጋር አካላት ጋር በመሆን በተገኘው የምርምር ዘዴ አባራሪና አጥማጅ /Push-pull/ ቴክኖሎጂ ዘዴን በመጠቀም ችግሮችን መከላከልና የአፈር ለምነትን መጨመር የሚያስችል ዘዴ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ይህ ዘዴም ሰብሎችን በስብጥር መዝራት እንደሆነ ከገለፃቸው ተረድተናል፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ፣ ሁለት እጁ እነሴ፣ ደጀንና ጐዛምን እንዲሁም ከጃቢጠህናንና ፍ/ሰላም ከተማ አስተዳደር የምስራቅና ምዕራብ ጐጃም ዞን የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የዞንና የቀበሌ ባለሙያዎች፣ የዘላቂ ልማት መካነ ጥናት አጋር አካላት፣ ዘጠኙ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድኑ አባላት፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የወርክሾፑ ተሳታፊዎች እንደነበሩ መረዳት ችለናል፡፡
