የኢትዮጵያ ሶስዮሎጂስቶች ሶሻል ወርከሮችና አንትሮፖሎጅስቶች ማህበር በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ወርክሾፕ አካሄደ

ደ/ማ/ዩ፡ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ሳይንስና ሂውማኒትስ ኮሌጅ ሶስዮሎጂ ትምህርት ክፍል ከኢትዮጵያ ሶስዮሎጂስቶች፣ ሶሻል ወርከሮችና አንትሮፖሎጅስቶች ማህበር ጋር በመተባበር ከሐምሌ14-16/2009 ዓ.ም የጥናትና ምርምር ክህሎትን ለማሳደግ በደ/ማ/ዩ የስብሰባ አዳራሽ ስልጠና አካሄደ፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ሳይንስና ሂውማንቲስ ኮሌጅ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የድህረ ምረቃ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ኃይሌ ካሳሁን የስልጠና መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ በጥናትና ምርምር ስራ ላይ የተሻለ ክህሎትና ዕውቀት መያዝ ለትምህርት ሰዎችና ተመራማሪዎች የጎላ ሚና እንዳለው ገልፀዋል፡፡ በገለፃቸውም ጥናትና ምርምር ማካሄድ በትምህርት ሙያቸው ላይ አዳዲስ የዕውቀት መሻሻሎችን መገብየት እንደሚችሉና ሌሎች ጠቃሚ የስልጠና መድረኮችን ማግኘት እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር ኃይሌ በንግግራቸው አክለውም የጥናትና ምርምር ስራዎች ባለሙያዎች የደረጃ እርከናቸውን ማሳደግ የሚያስችል ዋጋ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ መምህር የሆኑት ዶ/ር አስቻለው አበበ ስልጠናው ሲሰጥ የስልጠናው አርዕስት ደግሞ የጥናትና ምርምር ምንነትና ባህርያት፣ የአቀራረብ ዘዴዎች፣ ዓይነቶች፣ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችና የመረጃ አተናተን ስልቶች የሚሉትን አብይ ጉዳዮች አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሶሻልወርክ መምህር የሆኑት ዶ/ር ቀረብህ አስረስ በበኩላቸው የጥናትና ምርምር የፍልስፍና መሰረቶች፣ የምርምር አዘገጃጀት ሂደቶች፣ የመረጃና የናሙና አወሳሰድ፣ የመረጃ ትንተና እና ሌሎች ጉዳዮችን በስፋት አስረድተዋል፡፡

በስልጠናውም በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው ሰፊ ምላሽ እንደተሰጠ ከስልጠናው ለመገንዘብ ችለናል፡፡ ሶስዮሎጂስቶች፣ አንትሮፖሎጅስቶች እንዲሁም ሶሻል ወርከሮችና በነዚህ የትምህርት መስኮች የተመረቁ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎች ደግሞ የስልጠናው ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ በመጨረሻም ስልጠናውን በንቃት ተሳትፈው ለጨረሱ ሰልጣኞች የሰርቴፊኬት ሽልማት ተበርክቶ በግቢው በተለያዩ ቦታዎች የፎቶ ግራፍ ስነ-ስርዓት አካሂደዋል፡፡