ደ/ማ/ዩ፡-ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መማር ማስተማር፣ ምርምርና ሌሎች ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን ለመስራት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን ጥቅምት 3/2ዐ1ዐ ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው ሴኔት አዳራሽ የትብብር መድረክ በማካሄድ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነትና ትብብር ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሃይማኖት ዋሴ እንግዶችንና የፕሮግራሙን መርሃ ግብር ሲያስተዋውቁ እንደተናገሩት ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከበርካታ የሀገርና የውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ማዕከላትና ኢንዱስትሪዎች ጋር የትብብርና አጋርነት ሥራ እየሠራ እንደሆነ ገልፀዋል፤ አወያይተዋል፤ በባለቤትነትም ሠርተዋል፡፡
የትስስር መድረኩ ዓላማ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2ዐዐ9 ዓ.ም. የተፈራረሙትን የትብብርና አጋርነት ሰነድ በዝርዝር የሚያይና ወሳኝ ሁነቶች ዙሪያ በጥልቀት ሊሠራ የሚያስችል እንደሆነ ዶ/ር ኃይማኖት ገልፀዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ ጤናው ፕሮግራሙን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በ2ኛው ትውልድ የተመሠረተ የቅርብ ዩኒቨርሲቲ ቢሆንም በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎትና ሌሎች በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ገልፀዋል፣፡
ከመማር ማስተማሩና ምርምሩ ጋር በተያያዘ በተቋም ደረጃ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በ2ዐዐ9 ዓ.ም. በትብብርና አጋርነት ስራዎችን በጋራ እየሠራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በተለይም በጮቄ ተፋሰስ ዙሪያ የተሠሩ ሥራዎች እንዳሉም በመድረኩ አብራርተዋል፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋና ቀደምት ዩኒቨርስቲ በመሆኑ በቀጣይ በቅርበት ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለመስራት እንዲቻል የተዘጋጀ የስምምነት መድረክ በመሆኑ ዝርዝር ሥራዎችን በጥልቀት ያካተተ እና ቋሚ ፕሮግራም የያዘ መድረክ ነው ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የስምምነቱ አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳሁን ቱሬ በበኩላቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ስራ፣ ጥናትና ምርምርን ለማዳበር የአቅም ማጐልበቻ ስልጠና እና በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ በሚሉ ሶስት አበይት የትብብር መስኮች በጋራ እንደሚሠሩ ገልፀዋል፡፡ በተለይም በሕብረተሰብ ህይወት ዙሪያ የተጋረጡ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናት የማህበረሰብ አገልግሎት እየሠሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ያለበት የምስራቅ ጐጃም ዞን የስድስቱ ስነ-ምህዳራዊ ቦታዎች ያሉበት ዕድለኛ አካባቢ በመሆኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምረት በአካባቢ ጥበቃ ትምህርት፣ ጥናትና ምርምር ስራ እና ስልጠና የመሣሠሉትን ነገሮች እንደሚሠሩ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም በሁለቱ ተቋማት መካከል የጠበቀ ግንኙነት እየፈጠሩ የስራ ዝርዝሩን በዕቅድ አዘጋጅተው ወደ ተግባር የሚቀይሩ የግብረ ሃይል አባላትን ከሁለት ዩኒቨርሲቲዎች መርጠዋል፡፡ በዚህም ዶ/ር መስፍን አባተ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሰብሳቢ ሆኖ ሲመረጥ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ገነት ደጉ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እና ዶ/ር ካሳሁን ቱሬ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡ የስምምነት ሠነድም ተፈራርመዋል፡፡
