
ደ/ማ/ዩ፡-ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከጃፓይጐ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር አሳታፊ ስርዓተ ፆታን ያማከለ የመማር ማስተማር ስነ-ዘዴን ከጥቅምት 3-1ዐ/2ዐ1ዐ ዓ.ም. በጐዛምን ሆቴል ስልጠና ሰጠ፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ዲን ወ/ሮ ወርቅነሽ ጥሩነህ ስልጠናው በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ስር ለተቀጠሩ አዲስ፣ በዝውውር ለመጡና በሙያው ብዙ ቆይታ ለሌላቸው መምህራን ለትምህርት ጥራት የጐላ ሚና እንደሚኖረው ታስቦ ነው የተሰጠው፡፡
ስልጠናው የሚሠጠው ቀደም ብለው ስልጠናውን በወሰዱ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ መምህራንና ጃፓይጐ ኢትዮጵያ በተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በጥምረት ሲሆን ጃፓይጐ ኢትዮጵያ አዳራሽ ተከራይቶ፣ ቁሳቁሶችንና ሌሎች የሎጅስቲክ አቅርቦቶችን በማሟላት እንደሆነ ወ/ሮ ወርቅነሽ አክለው ገልፀዋል፡፡
በጃፓይጐ-ኢትዮጵያ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የትምህርትና ስልጠና አማካሪ አቶ መብት ከበደ በበኩላቸው ጃፓይጐ-ኢትዮጵያ ሴቭ ዘችልድረን/save the children / ከተሠኘ ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ግሮው ስሩ ኒወትሪሽን /Grow through nutrition/ የሚባል የ5 ዓመት /2ዐ16-2ዐ21/ የልማት ፕሮጀክት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም ፕሮጀክቱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የቅድመ ተግባር ትምህርት (Pre-service Education) በስርዓተ ትምህርት ማስፋፋት፣ በአቅም ማጐልበት ስልጠና፣ የአተገባበር ስነ-ዘዴን ማስፋፋትና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ እንደሚሠራ አቶ መብት ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ስልጠናው የመምህራንን አቅም በማጐልበት በትምህርት ጥራት ላይ አዎንታዊ እምርታን ለማምጣት እንዲቻል የመንግስት ስራን ለመደገፍ የሚሠራ ድርጅት በመሆኑ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲም የእቅዳቸው አንድ አካል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም በየጊዜው የሚቀጠሩትንና ሌሎች ስልጠናውን ያልወሠዱ መምህራንን እየተከታተሉ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመተባበር በትምህርት ጥራት ላይ የጐላ ስራ እንዲሠሩ አስተባባሪው ገልፀዋል፡፡
