ሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ደብተራ የተሠኘውን የግጥም መድብል አስመረቀ

ደ/ማ/ዩ፡- የኪነ-ጥበብ ባህል ዕድገትና ያልተነኩ የአካባቢውን ባህል ጥበቃ ልማት የሚሉ ሁለት ዓበይት ተልዕኮዎችን ሰንቆ የተነሳው የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም “ደብተራ” የተሠኘውን የግጥም መድብል ህዳር 2ዐ/2ዐ1ዐ ዓ.ም. በድምቀት አስመርቋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አንዳርጌ የምረቃት ስነ-ስርዓቱን በይፋ ሲከፍቱ እንደገለፁት ይህ የባህል ጥናት ተቋም የሙዚቃ፣ የስነ-ጽሁፍና የትያትር ክበብ አቋቁሞ ከዩኒቨርሲቲው እና ከውጭው ማህበረሰብ ተማሪዎችን በስነ-ጽሁፍ እና ስነ-ግጥም እያወዳደረ ይገኛል፡፡ በዚህም ረገድ የክበቡ አባል በሆነው በመምህር ደምሴ ደነቀው ተጽፎ የታተመው ደብተራ የተሠኘው የግጥም መድብል ለአንባቢያን አስተዋውቀዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጽሁፍ መምህር ዶ/ር ደመቀ ጣሰው የግጥም መድብሉን ተንትነው ለታዳጊዎች አቅርበዋል፡፡ በመሆኑም ባለደብተር/ፀሐፊ እና የሰረገላ ድባብ በሚል  “የደብተራን” ትርጉም ከመስጠት ጀምረው በግጥሙ ውስጥ የቀረቡትን ግጥሞች ጠቅለል ባለ መልኩ መልዕክታቸውንና ሌሎች መሠረታዊ የግጥም ትንተና        ላይ አስረድተዋል፡፡ ግጥሞች በቀላል ቋንቋ የቀረቡ፣ ጀሮ ገብ የሆኑ፣ በወል ግጥም የአፃፃፍ ስርዓት የቀረቡ እንደሆነም በባለሙያው ተብራርቷል፡፡ በተጨማሪም ደራሲው በህይወት ዘመናቸው ውስጥ ያሳለፉትን ትዝታዎች፣ ፀፀቶች፣ ምክሮች፣ ገጠመኞችና ሌሎች አስተማሪ ክስተቶችን በግጥሙ ውስጥ እንደሚንፀባረቁ እንዲሁም በይዘት ደረጃ የነከበደ ሚካኤልን የአፃፃፍ ስርዓትን የተከተሉ፣ ማህበረሰባዊ ሒስ ያላቸውና በይበልጥም የገጣሚውን ስሜት የሚገልፁ ቢሆኑም የአንባብያን ማንነትም የሚያስታወሱና ማንነታቸውንም በግጥሙ ትርጉም ውስጥ የሚያስገቡ እንደሆኑ ዶ/ር ደመቀ አክለው ገልፀዋል፡፡ ግጥሞች  ዘመን ተሻጋሪ፣ ተወዳጅ፣ ምክር ሰጭ እና ኢትዮጵያዊ ስነ-ግጥሞች ናቸው ተብሏል፡፡

የደብተራ የግጥም መድብል ገጣሚ መ/ር ደምሴ ደነቀው የግጥም አጀማመራቸውን፣ የነበሩትን ተግዳሮቶች እና ስኬቶችን በተመለከተ ከታዳሚው ከቀረቡላቸው በርካታ ጥያቃዎች ጋር በማዛመድ በዝርዝር ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡