የምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት የምርምር ዉጤቶችንና ቴክኖሎጂዎችን ለህብረተሰቡ እያሸጋገረ መሆኑን ገለፀ

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምሮችን እያካሄድ መሆኑን አስታወቀ፡፡ በምርምር ሂደቱም ያገኛቸውን አዳዲስ የምርምር ውጤቶችንና ቴክኖሎጂዎችን ወደ ማህበረሰቡ እንዲሸጋገሩ እየሰራ እንደሆነ አስረድቷል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ጌትነት አጥናፉ በዩኒቨርሲቲው መምህራን እየተሰሩ የሚገኙ አስራ ስድስት(16) የምርምር ስራዎች ከ2009 ወደ 2010 ዓ.ም የተሸጋገሩና ቀሪ 40% ስራቸው አልቆ የመረጃ ትንተና ስራቸው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ ከነዚህ በተጨማሪም ሁለት በልዩ ፍላጎት የሚሰሩ የምርምር ስራዎችም በሂደት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በ2010 በጀት አመት ለሚከናወኑ ስራዎች እቅድ በማዘጋጀት 130 ትልመ ጥናቶች በአዲስ መልክ ቀርበው በየደረጃው ከተገመገሙ በኋላ 99 የሚደርሱት ፀድቀው ወደ ስራ እንደገቡ ተገልጿል፡፡

ስለሆነም በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ 10፤ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ 18፤ ስነ-ትምህርትና ስነ- ባህሪይ ኮሌጅ 6፤ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 19፤ ምህንድስና ተቋም 14፤ ህክምና ትምህርት ቤት 7፤ ህግ ትምህርት ቤት 6፤ የቡሬ ግቢ 6፤ ሀዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም 6፤ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ 7 በጠቅላላው 99 ትልመ ጥናቶች ፀድቀው ወደ ስራ እንደገቡ ዶ/ር ጌትነት በዝርዝር አስፍረዋል፡፡

የምርምር ትልመ ጥናቶች ወደ ትግበራ እንዲገቡ የተደረገው የዩኒቨርሲቲውን የምርምር መመሪያ የትኩረት መስኮች መሰረት አድርጎ የምርምር ካውንስሉ በጋራ ከፀደቀ በኋላ ነው፡፡ በነዚህ ምርምሮች የሚሳተፉ ተመራማሪዎች ብዛት 295  ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ስድስቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጅ የሴት ተመራማሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን በመገንዘብ የምርምር አቅማቸውን ማጎልበቻ ስልጠና ለመስጠት ዳይሬክቶሬቱ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ዶ/ር ጌትነት አስረድተዋል፡፡