
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ከምስራቅ ጐጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር በዳሰሳ ጥናት ላይ የተመሠረተ ስለ ቅርስ አያያዝ፣ ማስተዋወቅና ጥበቃ በብቸና ከተማ የ2 ቀን ስልጠና ተሰጠ፡፡
የምስራቅ ጐጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃ ቱሪዝም ልማት የሥራ ሂደት አስተባባሪ ወ/ሮ ሙሉ አለማየሁ የስልጠናው አላማ በዞኑ የሚገኙ ቅርሶችን በተሻለ መንገድ ለመንከባከብ፣ ተገቢ ጥበቃ ለማድረግ እና ሰልጣኞች ስለቅርስ አያያዝና ጥበቃ ያላቸውን ግንዘቤ ለማዳበር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ደጀኔ ፍቅረማርያም በበኩላቸው ቅርስ የአንድን ሀገር ባህል፣ ታሪክና ስልጣኔን የሚገልጽና ሀገሪቱ ያላትን ድንቅ የተፈጥሮ ሀብት የሚያካትት ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ ስለሆነም ቅርሶች የአንድ ሀገር ህዝብ መታወቂያና መገለጫ ሆነው እንዲያገለግሉ በማልማት ለውጭ ምንዛሬና ተተኪውን ትውልድ ስላለፈው ህብረተሰብ ይበልጥ ለማሳወቅ ይረዳሉ፡፡ የህዝብን ብሔራዊ ስሜትንና የሀገር ፍቅርን በማጐልበትና ህብረቱን በማጠናከር የሀገርና የህዝብ መለያ በመሆን እንደሚያገለግሉም አክለው ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ በየነ ቸኮል በበኩላቸው ቅርስን ማስተዋወቅ ትምህርታዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማዎችን ለማሳካት በሚደረግ እንቅስቃሴ የጐላ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም የቅርሶች ጉዳት የሠው ልጅ ያሳለፈውን ታሪክ ወይም ስልጣኔ በትክክል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዳይተላለፍ ክፍተትን የሚፈጥር ሲሆን መንስኤዎች ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ስለሆነም ቅርስ ደህንነቱ እንዲጠበቅና እንክብካቤ እንዲደረግበት በተደራጀና ወጥነት ባለው መልኩ ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ መመዝገብ እንዳለበት ተገልጿል፡፡ የምዝገባ ሂደቱም ከተንቀሳቃሽ ቅርሶች ምዝገባና ከማይንቀሳቀሱ ቅርሶች መመዝገቢያ ቅፆች ላይ የቀለም ዓይነቱን፣ የተሠራበትን ቁስ፣ የቅርሱን መግለጫ፣ የአሰራር ይዘቱን፣ ልኬታና የመሳሰሉትን በትክክል በማስፈር መመዝገብ እንዳለበት የዩኒቨርሲቲው የታሪክና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ግዛቸው አንዳርጌ ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የህግ ት/ቤት መምህር አቶ አማረ ስጦታው በኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ህጐች ረጅም የሚባል ታሪክ ባይኖራቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ በተሻሻለ መልኩ ለቅርሶች የሚደረገው የህግ ከለላ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ ጥንታዊ ቅርሶች ላይ ብቻ የሚያጠነጥኑ የቀድሞ የቅርስ ጥበቃ አዋጆችም በተሻለ የማይዳሰሱ ቅርሶችን በማካተት የቅርስን ትርጓሜ ሰፋ በማድረግ ከለላ ሰጥቷል፡፡ እነዚህ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤን የሚመለከቱ ህጐችና ፖሊሲዎች ለሚመለከታቸው አስፈፃሚ አካላት በአግባቡ ተደራሽ ሆነው የቅርስ አስተዳደር በህግና መርህ የሚመራ መሆን አለበት ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ሰልጣኞች በበኩላቸው ቅርሶች በፊት ከነበራቸው አሁን የተሻለ እንክብካቤና የህግ ከለላ ያገኙ እንደሆነና ስልጠናው ቅርሶች በአግባቡ በጥንታዊ ይዘታቸው እንዲቀመጡና ለትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል፡፡ በርካታ ጥያቄዎችም ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ሰልጣኞችም በብቸና ዙሪያ፣ እናርጅ እናውጋ፣ ሸበል በረንታ፣ እነማይና ደጀን ወረዳዎች ላይ የተመረጡ ዳኞች፣ አቃቢ ህጐች፣ የባህል ቱሪዝም ሠራተኞች፣ የእስልምና ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የቤተክህነት ኃላፊዎችና የሙዚየም አስጐብኝዎች እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ወ/ሮ ሙሉ የቅርስ ባለይዞታ ተቋማት በተቋማቸው ያሉ ቅርሶችን ለአያያዝ ምቹ በሚሆኑ ቦታዎች በማስቀመጥ ማስተዋወቅ፣ መመዝገብ የሚገባቸውን ለሚመለከተው አካል ማስመዝገብ፣ የህግ አካላትም ህገወጥ የቅርስ ዝርፊያና ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የፍትህ አካላት፣ የሴክተር መስሪያ ቤቶችና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን በመስራት ቅርሶችን የማስተዋወቅ ስራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
