የህክምና ት/ቤት ለኢንተርንሺፕ ለሚወጡ ተማሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ተሰጠ

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ት/ቤት ከ4ኛ ዓመት ወደ 5ኛ ዓመት የገቡ የህክምና ተማሪዎች ወደ ተግባር ልምምድ (Internship) ከመሄዳቸው በፊት የብቃት ማረጋገጫ ፈተና (qualification exam) ተሰጠ፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ት/ቤት ለተማሪዎች የሚሰጠው የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ዋና አላማው ተማሪዎቹ በቀጣይ በደብረ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል ለሚያደርጉት የኢንተርንሺፕ ቆይታ ብቁ ሆነው በሌሎች ሀኪሞች ስር በመሆን በሽተኞቻቸውን ማከም መቻል አለመቻላቸውን ለማረጋገጥ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡ ፈተናው የተሠጠው በዩኒቨርሲቲው በሚያስተምሩ መምህራንና ከውጭ በመጡ ሐኪሞች እንደሆነ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ት/ቤት የህፃናት ህክምና ትምህርት ክፍል ተጠሪ ዶ/ር ኤርሚያስ አበባው አብራርተዋል፡፡

የብቃት ማረጋገጫውን የተፈተኑ የህክምና ተማሪዎች በቂ ውጤት ባያመጡና በአንድ የትምህርት አይነት ቢወድቁ የወደቁበትን የትምህርት ዓይነት ለ7 ሣምንታት ደግመው በመማር በዩኒቨርሲቲው መምህራን ፈተና ተሰጥቷቸው ወደ ተግባር ልምምድ ይገባሉ፡፡ የወደቁባቸው የትምህርት ዓይነቶች ሁለትና ከዚያ በላይ ከሆኑ ግን ዓመቱን በሙሉ በመድገም ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች እንደሚማሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለህክምና ተማሪዎች የተግባር ልምምድ የሚያስፈልገው በ4 ዓመት ቆይታቸው በንድፈ ሃሣብ (theory) ያገኙትን ዕውቀት በልምምድ ወደ ተግባር ለመቀየር ለማስቻልና ብቁ ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይ 13 ሳምንታትን በተግባር ልምምድ የሚቆዩ ተማሪዎች አንድ ሳምንት የዕረፍት ጊዜያቸው ሆኖ ሌሎቹ 12 ሳምንታት ግን የተግባር ልምምድ የሚያደርጉባቸው ጊዜያት ናቸው፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት መምህራን ለልምምድ የወጡ ተማሪዎችን ባዘጋጁት መስፈርት መሠረት በመገምገም 6 ወር ሲሞላቸው ያሳዩትን ጥንካሬ፣ የጨበጡትን ክህሎትና መስተካከል ያለባቸውን ነጥቦች በተመለከተ ለተማሪዎች ግብረ መልስ እንደሚሰጧቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ በ13ኛው ሳምንት መጨረሻ ደግሞ ተማሪዎችን በድጋሜ በመጥራት በ6ኛው ሳምንት የተሰጣቸውን ግብረ መልስ መሠረት አድርገው ያሣዩትን ለውጥ ይገመግማሉ፤ በሚደረገው ክትትል በተግባር ልምምዱ ብቁ ሆነው ካልተገኙ እንደገና በልምምዱ እንዲቀጥሉ እንደሚደረግ ዶ/ር ኤርሚያስ ተናግረዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ተማሪዎች ከተግባር ልምምድ ቆይታቸው በኋላ ሙያው የሚፈልገውን ክህሎት፣ ዕውቀትና አመለካከት በመጨበጥ እንዲሁም በጥሩ ሥነ ምግባር ታንፀው እንደሚወጡ ይጠበቃል ሲሉ ዶ/ር ኤርሚያስ አክለው ገልፀዋል፡: