የልዩ ችሎታ ማበልፀጊያ ማዕከል ተማሪዎች አቅማቸውን እንዲያጐለብቱ እያደረገ እንደሆነ ተገለፀ

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ችሎታ ማበልፀጊያ ማዕከል የተለየ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ለማበረታታትና ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር 5 ሞዴል ወረዳዎችን በመምረጥ በወረዳው ለሚኖሩና በሳይንሱም ሆነ በቴክኖሎጂው የተለየ ችሎታና ተሰጥኦ ላላቸው አካላት ስልጠና ለመስጠት የስልጠና ማንዋል በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡

በምስራቅ ጐጃም ዞን በዞን ደረጃ በተደረገው ውድድር የተሻለ ተሳትፎ ያሳዩና በርካታ ተማሪዎችን ይዘው የተገኙ ወረዳዎች እንደ ሞዴል ተደርገው ተመርጠዋል፡፡ ወረዳዎቹ ቢቸና፣ ሉማሜ፣ የጁቤ፣ ረቡ ገበያ እና ድጐ ሲሆኑ በነዚህ ወረዳዎች ማዕከል ለማቋቋምና ተማሪዎችን ለማጠናከር በየወረዳው ያሉ በሳይንሱም ሆነ በቴክኖሎጂው የተለየ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸው መምህራን፣ የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች እና በዞን ደረጃ ያሉ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ወደ ሥራ ለመግባት የስልጠና ማንዋል በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ባሉ መምህራን እየተዘጋጀ እንደሚገኝ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ችሎታ ማበልፀጊያ ማዕከል ኦፊሰር አቶ ገበየሁ ሽፈራው አብራርተዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ችሎታ ማበልፀጊያ ማዕከል የሚገኙ ተማሪዎች በፊት የነበራቸውን እውቀትና ክህሎት እንዲሁም ተሰጥኦ የበለጠ እንዲያጐለብቱ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ግብዓቶችንና መስሪያ ቦታዎችን አመቻችቶላቸዋል፤ የማጠናከሪያ ትምህርትም እሁድና ቅዳሜ እንደሚሰጣቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

ተማሪዎች ከሠሯቸው ስራዎች ውስጥ ጥቂቶቹ የሌባ መቆጣጠሪያ፣ ሙቀትን ለመከላከል የሚያስችል ሄልሜት፣ በሶላር የሚሠራ መኪና፣ በተራሮች አካባቢ የሚከሰት አደጋን ለመቀነስ የሚያስችል፣ የእንቦጭ አረምን በቀላሉ ለመሰብሰብ የሚያስችል ጀልባ፣ የቤት ውስጥ ቆሻሻ ማጽጃ፣ የውሃ ማጣሪያና ማቀዝቀዣ፣ የብር ማቅለጫ፣ የቤት ስርቆትን ለመላከል የሚያስችል መሳሪያ፣ የካልኩሌተርና የእንግሊዝኛ አጋዥ መጽሐፍ ሶፍትዌር የተለያዩ ኮዶችን በማዘጋጀት፣ ሶላር ስቶቭና የመሳሰሉት እንደሆኑ ለማየት ተችሏል፡፡

የተሰሩ ስራዎችንም በተለያዩ መገናኛዎች የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል፡፡ ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች አካላት የበለጠ ለማስተዋወቅ በቅርቡ በዩኒቨርሲቲው ኢግዚቪሽን እንደሚካሄድ አቶ ገበየሁ ሽፈራው ገልፀዋል፡፡

በማዕከሉ የሚሳተፉ ተማሪዎች ወደ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በመምጣታቸው በተለያዩ ግብአቶች አለመሟላት የሚያቋርጡት የነበረውን ሥራ የበለጠ አጠናክረው እንዲሠሩ እንዳስቻላቸውና በመደበኛ ትምህርታቸው ላይ በሚሰጠው ማጠናከሪያና በሚደረገው የፉክክር መንፈስ ለውጥ ማምጣት መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ችሎታ ማበልፀጊያ ማዕከል ኦፊሰር አቶ ገበየሁ ሽፈራው ስልጠናው ከተሰጠ በኋላ ለወደፊት ከተለያዩ አካላትና ት/ቤቶች ጋር የበለጠ ተነጋግረው እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡