
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህግ ት/ቤት አሚከስ ሚዲያ ፕሮሞሽንና ኮሚኒኬሽን ጋር በመተባበር “ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው እና ሌሎች የፌደራሊዚም አማራጮች ለብሔር ግንባታ /Nation building/ ያላቸው ፋይዳ በንጽጽር” በሚል ርዕስ ተማሪዎችን ያሳተፈ በመምህራን መካከል የካቲት 22/2ዐ1ዐ ዓ.ም. ክርክር ተካሄደ፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህግ ት/ቤት ዲን አቶ ወልደተንሳኤ ፈንቴ እንደገለፁት የክርክሩ አላማ ተማሪዎች በንድፈ ሃሣብ የተማሩትን ትምህርት እንዴት እንደሚጠቀሙ ለመፈተሽ፤ ሀሣብን በነፃነት የሚገልጽና ተከራክሮ የሚያሳምን ዜጋን ለማፍራት እንዲያስችል እና በዩኒቨርሲቲዎች የክርክርን ባህል በተማሪዎች መካከል ለማዳበር ነው፡፡
ከተከራካሪዎች አንደኛው ቡድን የብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ለሀገሪቱ ያለውን ጠቀሜታ በመግለጽ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝምን በመደገፍ ሲከራከር ተቃራኒው ተከራካሪ ቡድን ደግሞ የብሔር ተኮር ፌደራሊዝም የሚያስከትለውን ተጽዕኖ በመግለጽ ሃሣቡን ተቃውሞ በሌላ አማራጭ ፌደራሊዝም ሥርዓት መመራት አስፈላጊ እንደሆነ ሃሳባቸውን በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡
ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች ክርክራቸውን ከጨረሱ በኋላ በዳኞች ከተዘጋጁ ጥያቄዎች ለእያንዳንዱ ተከራካሪ ቡድን አንድ አንድ ጥያቄ ተጠይቆ ተከራካሪዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ዳኞች የተከራካሪ ቡድኖችን ውጤት ከለዩ በኋላ በአሚካስ ሚዲያ ፕሮሞሽንና ኮምኒኬሽን የተዘጋጀ ሽልማት ለእያንዳንዳቸው ተከራካሪዎች ተበርክቶላቸዋል፡፡
በመጨረሻም ክርክሩ ተማሪዎችን በማሳተፍ ቀጣይነት ኑሮት ለሁሉም የህግ ተማሪዎች በማዳረስ በንድፈ ሃሣብ የተማሩትን በተግባር ልምምድ እንዲያደርጉና ሃሳባቸውን በነፃነት መግለጽ እንዲችሉ ቢደረግ ጥሩ ነው ሲሉ ተከራካሪዎች አሳስበዋል፡፡
