
ደ/ማ/ዩ፡- በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጮቄ ተፋሰስ ምርምርና ልማት ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በ13 የልቅና ማዕከላት ለታቀፉት አርሶ አደሮች አስተዋወቀ፡፡
በዚህም ረገድ አዳዲስና የተሻሻሉ የእርሻ መሣሪያዎች ተገዝተው ለአርሶ አደሮች ይደርሱ ዘንድ ሚያዝያ 16/2ዐ1ዐ ዓ.ም. ለአርሶ አደሮችና ለባለሙያዎች የቀለምና የተግባር ስልጠና ተሠጧል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ገነት ደጉ በስልጠናው ተገኝተው እንደተናገሩት ጮቄን ወደነበረበት ለመመለስ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን ለመነሻነት በመስራት ለአካባቢው ማህበረሰብ አማራጭ ቴክኖሎጅዎችን ለማምጣት ዳይሬክቶሬቱ ሲሠራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ሆኖም የአካባቢውን ማህበረሰብ ወደተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ለማድረስ በተቀናጀ የተፋሰስ ስራ ማዘመን በማስፈለጉ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ስራዎችን እየሠሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ለዚያም ስልጠናው መሠረታዊ ስለሆነ ሠልጣኝ አርሶ አደሮች በንቃት ተሳትፈው የበለጠ ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ህይወታቸውን በኢኮኖሚ አዳብረው ቴክኖሎጂውን ለሌሎች እንዲያደርሱ አሳስበዋል፡፡
በአዲስ አበባ የአይባር ኢንጅነሪንግ ስራ አስኪያጅና ተመራማሪ ዶ/ር መለሰ ተመስገን በሶስት መሠረታዊ የእርሻ መሣሪያዎች ላይ ያተኮረ ስልጠና እንደሠጡ ተገንዝበናል፡፡ ይህም በርከን ማረሻ በባህላዊ ማረሻ ላይ የሚገጠም፣ የአርሶ አደሩን ድካም የሚቀንስ፣ የአፈር መከላትንና ጐርፍን የሚቀንስ፣ የበሬውን ጉልበትና የእርሻ ድግግሞሽን በመቀነስ ምርትን የሚጨምር መሣሪያ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ሁለተኛው ስንጥቁ አይባር ቢቢኤም ከበፊቱ የቁጥጫ አፈር ማጠንፈፊያ በአይነቱ የተለየ ሲሆን ሁለተኛ ትዉልድ መሣሪያ በመባል እንደሚጠራ በመግለጽ በዝናብ አጠርም ይሁን በዝናባማ አካባቢ መጠቀም የሚችል መሣሪያ ነው፡፡ ሶስተኛው በመስመር መዝሪያ መሣሪያ ሲሆን በአንድ ጊዜ በአምስት መስመር ዘሩንና ማዳበሪያውን መዝራት የሚያስችል መሣሪያ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ይህም በአንድ ጊዜ የ1ዐ አርሶ አደሮችን ጉልበት የሚቀንስ አዲስና የተሻሻለ መሣሪያ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ስለሆነም ሶስቱ መሣሪያዎች የአርሶ አደሩን ድካም በመቀነስ፣ አፈር በጐርፍ እንዳይታጠብ የሚያግዙ፣ የበሬውን ጉልበት በመቀነስ የአፈርን መከላት ይቀንሳል፡፡ ለድግር ተብሎ የሚጨፈጨፈውን የደን መራቆትን በመቀነስ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ይሠጣሉ፡፡ እንዲሁም ባላቸው ዘመናዊነትና ለአርሶ አደሮች በሚሠጡት ጥቅም ከበፊቱ ማረሻዎች በከፍተኛ ሁኔታ ልዩነት ስላላቸው አርሶ አደሩ በፍጥነት ቴክኖሎጂዎችን ተቀብሎ ወደ ስራ ሊገባ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሰልጣኝ አርሶ አደሮችም በጆሯቸው የሠሙትን የእርሻ መሣሪያዎችን በተግባር በማየታቸዉ ደስታቸውን በመግለጽ በፍጥነት ቴክኖሎጂውን ተቀብለው ለሌሎችም እንደሚያደርሱ ገልፀዋል፡፡ ይህንንም በተለያዩ የገበሬ በዓላት ተጠቅመው አርሶ አደሩን ወደ ስራ እንደሚያስገቡ ገልፀዋል፡፡
