የተበጣጠሠ መሬትን ገጣጥሞ ካርታ በመሥራት ምርትና ምርታማነትን መጨመር እንደሚቻል ተገለፀ

ደ/ማ/ዩ፡- ደ/ማ/ዩ፡-የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ተቋም በአፒር /APPEAR Project/ አማካኝነት ለ18 ባለሙያዎችና ለመሬት አስተዳደር 2ኛ አመት ተማሪዎች ስልጠና ሰጠ፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ተቋም ዲን አቶ ንጉስ አዳነ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ተቋም እና ኦውስትሪያ ሀገር ከሚገኙ TUW እና BOKU ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተጀመረው ፕሮጀክት አማካኝነት ለመሬት አስተዳደር ባለሙያዎችና ከመሬት ካርታ ስራ ጋር የተገናኘ ስራ ላላቸው መምህራንና ሙያተኞች ስልጠናው እንደተሰጠና በስልጠናው ከዞን፤ ከወረዳና ከዩኒቨርሲቲው ከጂኦግራፊ፤ ግብርናና ምህንድስና የትምህርት ክፍሎች የተውጣጡ ሙያተኞች መካፈላቸውን ገልፀዋል፡፡

አቶ ንጉስ አዳነ እንደገለፁት የተበጣጠሠ መሬትን መገጣጠምና ካርታ ሥራ በስልጠናው የተካተቱ በመሆኑ የዚህ አይነት ስልጠና የተበጣጠሠ መሬት ባላቸው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተበጣጠሠ መሬትን በመገጣጠም ግልጽና የማያሻማ የመሬት ካርታ በመስራት ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ ከእርሻ መሬት ጋር ተያይዞ የሚፈጠርን አለመግባባትና የመልካም አስተዳደር ችግር መቅረፍ እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ለ2ኛ አመት የመሬት አስተዳደር ተማሪዎች ከኦስትሪያ ሀገር በመጣ ልምድ ባለው ፕሮፌሠር አማካኝነት ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት ያህል የፎቶግራሜትሪ ኮርስ የተሠጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስልጠናውም በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተደገፈ በመሆኑ ተሣታፊዎች ስልጠናውን በአግባቡ መከታተል እንደቻሉ አቶ ንጉስ አዳነ አስረድተዋል፡፡

ተሳታፊዎች በበኩላቸው በተግባር የተደገፈ ስልጠና በመሠጠቱ ክህሎታቸውን እንደሚያሳድግ እና በሠለጠኑት ስልጠና መሠረት በአካባቢያቸው በመሄድ እንደሚተገብሩ ገልፀው ወደፊት ሥልጠናዎች ሲዘጋጅ ከሀገር ውስጥ ልምድ ያላቸው ምሁራንም ተካተው ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ያገናዘበ ሥልጠና መሰጠት ቢቻልና የክትትልና ድጋፍ ሥርዓት ቢዘረጋ በማለት አስተያየታቸውን ሠጥተዋል፡፡