የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሜጋ ፕሮጀክት ትልመ ጥናት ወርክሾኘ አካሔደ

ደ/ማ/ዩ፡- ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራንና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የሜጋ ፕሮጀክት ትልመ ጥናት ውይይት አካሄደ፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማ/አገልግሎት ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶ/ር ምህረት አለማየሁ ጮቄ ተፋሠስ በርካታ ሥነ ምህዳር ያለው፤ የበርካታ ወንዞች መነሻ እና የበርካታ ሥነ ህይወት መገኛ ነው፡፡ ሆኖም ግን በተለያዩ ጊዜያት የተጠኑ ጥናቶች ሥነ ምህዳሩ እየተዛባ መምጣቱንና በርካታ ሥጋቶች የተደቀኑበት መሆኑን እንደሚያመለክቱ በመጥቀስ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ስጋቶችን ለመቅረፍ በርካታ የምርምር ሥራዎች እየሠራ እንደሆነ በዚህም 4 /አራት/ ቡድኖች ተቋቁመው በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ የብዝሃ ህይወትና አካባቢ ጥበቃ፤ የውሃ፣ የመስኖና ኢነርጅ ልማት እንዲሁም ኢኮ ቱሪዝም ልማት በሚሉ የትኩረት መስኮች ላይ የፕሮጀክት ፕሮፖዛሎችን እየሰሩ ሲሆን ሁለቱ ሜጋ ፕሮጀክት ትልመ ጥናቶች ተጠናቀው ለግምገማ እንደበቁ አስረድተዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶ/ር ታፈረ መላኩ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የትኩረት መስክ ካደረጋቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ጮቄን የምርምር ማዕከል ማድረግ በመሆኑ የቀረቡት ሁለት ሜጋ ፕሮጀክት ፕሮፖዛሎች በጮቄ ላይ የተደቀኑትን ሥጋቶች የሚቀንሡ በመሆናቸው በተሣታፊዎች በሚቀርቡ ተጨማሪ ሃሳቦች ዳብረው ወደ ትግበራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

በወርክሾፑ የሜጋ ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ያቀረቡት ዶ/ር አረጋ ሙሉ የፕሮጀክት ፕሮፖዛሉን ከመፃፋቸው በፊት በ16 የጮቄ ተፋሠስ ወረዳዎች በመዟዟር መረጃዎችን በመሠብሠብ ዋና ዋና ችግሮችን በመለየት የፕሮጀክት ትልመ ጥናት በቡድን ማዘጋጀት እንደቻሉ ገልፀዋል፡፡

የፕሮጀክት ትልመ ጥናቱ በጮቄ ተፋሠስ ላይ ያተኮረበት ምክንያት ለዩኒቨርሲቲው ቅርብ በመሆኑ? በርካታ አካባቢዎችን ስለሚሸፍን፣ በርካታ ሥነ ህይወት መገኛ በመሆኑ፣ በርካታ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ እና በርካታ ሥራዎችን መስራት የሚያስችል አቅም ስለአለው እንደሆነ ዶ/ር አረጋ ሙሉ አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም በባለሙያዎች የሚሠጡ አስተያየቶችን በመጨመር እና ልምድ ያላቸውን ምሁራን በማሳተፍ በ2ዐ11 ወደ ትግበራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡