ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ 28ሺ 4ዐዐ ዶላር የሚያወጡ የህክምና መሣሪያዎች ድጋፍ አገኘ::

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጃፓይጐ ኢትዮጵያ ከሚባል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የህክምና ትምህርትን በተግባር ለመስጠት የሚያግዙ የ28 ሺ 4ዐዐ አሜሪካን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገለት፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ ጤናው በስነ-ምግብ የትምህርት ዘርፍ ዩኒቨርሲቲው ሲከፍት የተግባር መስጫ መሣሪያዎች ለማሟላት በሂደት ጥረት ማድረጋቸውን ጠቁመው ጃፓይጐ ኢትዮጵያ ያደረገው ድጋፍ ለመማር ማስተማሩ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

አቶ ታደሰ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ሁሉም የትምህርት ክፍሎች የተደራጀ የቤተ-ሙከራ ዕቃዎች እንዲኖራቸውና የተሟሉ ለማድረግ እንደ የግብዓት አቅርቦት ሁኔታቸው ቅደም ተከተል ወጦላቸው በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ ግርማው ዓለም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከጃፓይጐ ኢትዮጵያ ያገኘው ድጋፍ ዓለም አቀፍ የሆኑ ምርምሮችን ለመስራት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡

በጃፓይጐ ኢትዮጵያ የ“ግሮው ስሩ ኒውትሪሽን” የቅድመ አገልግሎት ስልጠና የትምህርትና ስልጠና አማካሪ አቶ ከፍያለው ሙለታ ድጋፉ በተሰጠበት ወቅት ጃፓይጐ ከስምንት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ቤተ ሙከራዎችን በማጠናከር የትምህርት ጥራትን ከማምጣትና ከማረጋገጥ፣ በስርዓተ ትምህርት ቀረፃ ላይ በመሳተፍ እንዲሁም የመምህራንና የቤተ-ሙከራ ባለሙያዎችን አቅም ግንባታ ላይ እየሠራ መሆኑን አስታውሰው ድጋፉ የተደረገው ቤተ-ሙከራዎችን ለማጠናከር ነው ብለዋል፡፡

አቶ ከፍያለው አያይዘውም የትምህርት ሚኒስቴርና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እየተሠሩ ካሉ ስራዎች መካከል አንዱ ቤተ ሙከራዎችን ማደራጀት ሲሆን ተማሪዎች የህክምና መሣሪያዎች በመላመድ ተግባር ተኮር ዕውቀት እንዲገበዩና ምርምርን ቀልጣፋና አስተማማኝ ለማድረግ ይጠቅማሉ ብለዋል፡፡ ድጋፍ የተደረጉት መሣሪያዎችን አጠቃቀም በተመለከተ በቂ ገለፃ በወቅቱ ተሰጥቷል፡፡

በቀጣይም ከግብርናና የጤና ሳይንስ ኮሌጆች ጋር በስነ-ምግብ ላይ ምርምሮችንና የስርዓተ ትምህርት ቀረፃ ላይ እንደሚሠሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡