ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለደብረ ማርቆስ ከተማ መብራት ዝርጋታ ሙያዊ ድጋፍ አደረገ::

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፉ በተለያዩ ጎጃም አካባቢዎችና በተለይም በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ችግር ፈች የሆኑና የማህበረሰቡን ህይወት ሊያሻሽሉ የሚችሉ አገልግሎቶችን ፍላጎትንና ጥያቄን መሰረት እያደረገ ይሰጣል፡፡

ለዚህም ማሳያ በደብረ ማርቆስ ከተማ ለተሰራው የ6.4 ኪ.ሜ የመንገድ መብራቶች ዝርጋታ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግማሽ ሚሊዮን ብር ሊያወጣ የሚችል ሙያዊ ድጋፍ በዓይነት ማድረጉ ነው፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ተቋም የኤሌክትሪካል ምህንድስና መምህር እና በዩኒቨርሲቲዉ የግንባታ ፕሮጀክት ፅ/ቤት የኤሌክትሪክ መሃንዲስ አቶ ጌትየ ወልደፃድቅ ዩኒቨርሲቲዉ ከከተማ አስተዳድሩ ጋር በተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቶ ጌትዬ ደብረ ማርቆስ ከተማ በመንገድ መብራት ዝርጋታዉ ዙሪያ በከተማዉ ዉስጥ በተለያዩ የመንገድ ሳይቶች ላይ የመብራት ዝርጋታ ዝርዝር መግለጫ ከማዉጣት ጀምሮ እስከ ፍፃሜዉ ድረስ ስራዎችን በመከታተል ሙያዊ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት አስተዋፅዖ ማህበረሰቡን በእጅጉ ያስደሰተ ተግበር ሲሆን በተለይም የግዥ ስፔስፊኬሽን በማውጣት እና ያንን ተከታትሎ በመስራት በኩል ሊከሰት የሚችለውን የጥራት ጉድለትና የሃብት ብክነትን ለማስቀረት እንደሚረዳ በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማት የቤቶችና መሰረተ-ልማት ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ እንዳልካቸዉ ሙሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ እንዳልካቸው አያይዘውም ደብረ ማርቆስ ከተማ በ2010 በጀት ዓመት አዲስ የመንገድ መብራት ፕሮጀክት ከከተማ አስተዳድሩ የዉስጥ ገቢ 21.3 ሚሊዮን ብር በማስመደብ የመንገድ መብራቱን በመስራት ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅርበት በመስራት የመብራቱን ስራ ዲዛይን በማዉጣትና በሂደቱ ላይ ክትትል በማድረግ ኤሌክትሪካል በሆኑ ጉዳዮች ላይ ላደረጋቸዉ ሙያዊ ድጋፍ አቶ እንዳልካቸዉ ምስጋናቸዉን ቸረዋል፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ ሙያዊ ድጋፍ ለሚፈልጉ አካላት ሁሌም በሩ ክፍት እንደሆነም አስታውቋል፡፡