
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ኦስትርያ ከሚገኘዉ ጆንስኬፕለር ዩኒቨርሲቲ ጋር አብሮ መስራት ጀመረ፡፡
ከጆንስኬፕለር ዩኒቨርሲቲ በመጡ ሁለት ፕሮፌሰሮች ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡
በወቅቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የዉጭ ግንኙነትን በማጠናከር ዩኒቨርሲቲዉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚሆንበትን አሰራር ለመዘርጋት በትኩረት እንደሚሰራበት ተናግረዋል፡፡
ትምህርቱን የሰጡት ፕሮፌሰር ማይከል ጆን ኦስትርያና ኢትዮጵያ ረጅም የግንኑነት ታሪክ ያላቸዉ ሃገራት እንደመሆናቸዉ በአሁኑ ሰዓት በደንብ ተጠንተዉ መቅረብ የሚገባቸዉ ርዕሰ ጉዳዮችን በመለየት ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
በዘመነ ሉላዊነት በተለይም በአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ወደ አለም አቀፍ ዜግነት መምጣት የወቅቱ የዓለማችን ትልቁ አጀንዳ ስለሆነ ሁሉም ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል ሲሉ ፕሮፌሰር ቪትዋን ተናግረዋል፡፡
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከጆንስኬፕለር ዩኒቨርሲቲ ጋር በምርምር፣ በተማሪና መምህር ልዉዉጦች በስኮላርሽፕና መሰል አካዳሚክ ግንኙነቶች የመግባቢያ ሰነድ በቅርቡ በመፈራረም ወደ ስራ ይገባል፡፡
ከሀገር ዉስጥና ከዉጭ ያሉ የምርምር አቻ ተቋማት እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች ጋር የአጋርነት ስራዎች ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉም ተጠቁሟል፡፡
