
የደማዩ፡-ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጮቄ ተፋሰስን ልማት ለማፋጠን ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራን አስመልክቶ የአካባቢዉን ማህበረሰብ ጨምሮ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የክልል ቢሮ ሃላፊዎች እና ግብረ ሠናይ ድርጅቶች በተገኙበትየውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡
ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የማነቃቂያ ንግግር (keynote speech) ያደረጉት ወ/ሮ ዉቧ መኮነን ተፈጥሮን ካልጠበቅናት ልትጠብቀን ስለማትችል ራሳችንን አደጋ ላይ እንጥለዋለን፡፡ ስለሆነም ሁሌም ተፈጥሮን እንዳገኘናት መጠቀም ብቻ ሳይሆን መጠበቅ ይገባል ብለዋል፡፡ እና የፌዴራል የብዝሃ ህይዎት ማትጊያ እና ማካተቻ ስራ አስኪያጅአቶ አብዴታ ደበላ ስለ ብዝሃህይዎት ማትጊያ እና ማካተቻ ፕሮጀክት እንቅስቃሴ ላይ የጮቄ ተራራ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተፋሰሱ ላሉ ሀገሮች ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳደረገ ገልጸዉአሁን ስላለበት ሁኔታ የዳሰሳ ጥናት ሲያቀረቡ አስራ አራት ወረዳዎች በማደራጀትና የምግብ ዋስትናቸዉን ለማረጋገጥ ከተፈጥሮ ሀብት ጋር የማዛመድ ስራ ተሰርቷል ብለዉ የስርዓተ-ምህዳርን አገልግሎት ክፍያ የዚህ ፕሮጀክት ትልቁ ግብ መሆኑን ጨምረዉ አስረድተዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የጮቄ ተፋሰስ ምርምርና ልማት ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርአቶ አብዮት ሞላ ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በጮቄ ተራራ እና ተፋሰስ በተለያዩ መንገዶች የጥበቃ ሥራዎችን በማከናወን ሌሎችም እንዲሳተፉበት የማስተዋወቅ ሥራ መሰራቱን አስታውቋል፡፡፡ በተጨማሪ ዳይሬክቶሬቱ የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ዘዴዎች በተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ስራ፣ በሰብል ልማት፣ በእንስሳት መኖ እና በአትክልትና ፍራፍሬ የመሳሰሉት ስራዎች እንደተሰራ ገልጸዋል፡፡
የምስራቅ ጎጃም ዞን የገጠር መሬት አስተዳድር መምሪያ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ደሳለኝ ስለ ጮቄ ተራራ ታሳቢ ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራን አስመልክቶ የልምድ ልዉዉጥ አስፈላጊነትና ቅመራን ወደ ማህበረሰቡ የማሳደግ ስራ የአከላል ሂደትና የሰነድ አየያዝ እንዲሁም ጥብቅ ስፈራዉን ከአደጋ ለመከላከል ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተወሰዱትን መፍትሄዎችን በተመለከተ አብራርተዋል፡፡
ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ የቀድሞዉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፣አቶ አብርሃም አለኸኝ የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና አቶ ከበደ ይማም የፌዴራል የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለዉጥ ም/ኮሚሽነር ስለ ጮቄ ተራራ ታሳቢ ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራን አስመለክቶ ከአካባቢዉ ከመጡ ማህበረሰቦች ጋር የጋራ ወይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ክቡር ርዕሠ መስተዳድሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጮቄን መጠበቅ መጀመሪያ ሃላፊነቱም የማህበረሰቡ ነው፤ ማህበረሰቡ ጮቄን ካልጠበቀ የመጀመሪያው ተጎጅ የአካባቢው ማህበረሰብ ነው፤ ስለሆነም ጮቄን የመንግስት ሳይሆን የራሳችሁ ህልውና ጉዳይ አድርጋችሁ ልትጠብቁት ይገባል፤ መንግስትም ከጎናችሁ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
