አድዋ የታሪክ እይታና የሠውን ልጅ ፍልስፍና የቀየረ ክስተት እንደሆነ ተገለፀ

የደ/ማ/ዩ፡-123ኛዉን የአድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ ̎የአድዋ ድል ለሃገራዊ ፍቅር እና አንድነት ̎ በሚል መሪ ቃል በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አዉደ ጥናት ተካሄደ፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ በመክፈቻ ንግግራቸው የአድዋ በዓል ሀገራዊ አንድነትን ያሳየ ትልቅ የድል በዓል መሆኑን ጠቅሰዉ የሚገባዉን ክብር ባለመስጠታችን በትውልድ መካከል የሚታይ ክፍተት እየፈጠረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አሁን ያለዉ ትዉልድ አያቶቻችን አጥንታቸዉን ከስክሰዉ ደማቸዉን አፍስሰዉ ከቀኝ ግዛት ባርነት ስላዉጡን ተገቢዉን ክብር ልንሰጣቸዉ እኛም እንደትውልድ ያለብንን ሃላፊነት በአግባቡ ልንወጣ ይገባል በማለት መልክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡

በአዉደጥናቱ የአደዋ ድል ሚስጥር በሚል ርዕስ አንኳር ንግግር ያቀረቡት ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ የአድዋን ጦርነት ላይ አጼ ምኒሊክ በመሩት የኢትዮጵያ አርበኞች ገድል የፋሽስት ጣሊያን ጦር ድል ያደረጉበትን  ሚስጥር በስፋት ተወስቷል፡፡

ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ‹‹በአድዋ ላይ ማንነትን›› በተመለከተ ወግ የቀረበ ሰሆን የአደዋ ድል በማንነቱ በኢትዮጵያነቱ የማይደራድር ዜጋን ለመፍጠር  ያላቸው አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አድዋ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ካለ ማማ ላ ያስቀመጠ ብሔራዊ ኩራታችን እንደሆነም በሰፊው ተወርቷል፡፡

‹‹የአድዋ ድልና የታሪክ አሻራዉ›› በሚል አርዕስት ጥናታዊ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን የአድዋ ድል ትቶት የሄደዉን ዘላለማዊ አሻራ አሁን ያለዉ ትዉልድ ከአድዋ ድል ታሪክ ምን መማር እንዳለበት እና የመሳሰሉ ነገሮች ከተነሳ በኋላ ቅደመ አድዋ፣ድህረ አድዋ በሚል  የአድዋ ጦርነት ከመካሄዱ በፊትና ከተካሄደ በኋላ ያለዉን የጦርነቱን መነሻ መንስኤዎችና ጦርነቱ ያስከትለዉን ዉጤት መሰረት ያደረጉ ነጥቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

አርበኝነት ለኢትዮጵያ አንድነት ያበረከተዉን አስተዋጽዖ ‹‹የአበሻ ጀብዱ›› የሚል መጽሀፍ ላይ የተደረገ ቅኝትም ቀረበ ሲሆን አርበኝነት እንደኢትዮጵያ ላሉ ዘመናቸውን ለኖሩበት የማይገሰስ የኩራት መገለጫ እንደሆነ ቀርቧል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ ጥናታዊ ፅሁፎች በተጨማሪ ግጥም፣ ቅኔ፣ እና መነባንብ ቀርቧል፡፡