ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሃፍት ኤጀንሲና ከአማራ ክልል ባህል ቱሪዝምና ፓርኮች ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ‹የጎጃም መዛግብት› በሚል ርዕስ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ግዛቸው አንዳርጌ በመክፈቻ ንግግራቸው ‹‹የዩኒቨርሲቲውን ተልዕኮዎች ለማሳካት የተደራጀ ቤተ-መፅሐፍት መኖሩ አስፈላጊ በመሆኑና ያለንበት ዘመን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመን በመሆኑ፤ ቤተ-መፅሐፍቶቻችንን ወደ ዲጂታል ዘዴ መቀየርና መፅሐፍትና መዛግብትን ዲጂታይዝድ በማድረግ ለአንባቢያን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዲጂታል ቤተ-መፅሐፍት አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ የውይይት መነሻ ፅሑፍ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሐፍት ኤጀንሲ የመረጃ ቋት አስተዳደር ባለሙያ በሆኑት በአቶ ግዛው ዋቅጅራ እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ የህትመት አዘገጃጀትና አሰባሰብ ዙሪያ ሌላ የውይይት መነሻ ፅሑፍ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጽሃፍት ኤጀንሲ የመረጃ ሃብቶች አስተዳደር ዳይሬክተር ወ/ሮ ሙሉእመቤት ጌታቸው ቀርቧል፡፡

ደረጃውን የጠበቀ አለማቀፍ የህትመት አዘገጃጀትና አሰባሰብ ላይም ከውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየትና ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ በምስራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ባለሙያ የሆኑት አቶ በልስቲ ብርሃን የነጻ ህትመት አሰጣጥ መመሪያው ላይ ብዥታ መኖሩን ጠቁመው በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ደራሲ ነኝ በሚልበት ሁኔታ ብዙ ሰዎች ለህትመት የማይበቃ ስራ እያመጡ መፅሐፍ አሳትመናል ሽጡልን እያሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህንን መሰል ጥያቄ የሚስተናገዱበትን ህጋዊ ማዕቀፍ በተመለከተም ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

የዚሁ ዝግጅት አካል የሆነ በደብረ ማርቆስ ከተማ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት አደባባይ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ  ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ይህይስ አረጉ ፣ የምስራቅ ጎጃም ዞን ባህል ቱሪዝም ሃላፊ  ወ/ሮ ውዳላት አልማው፣ የምስራቅ ጎጃም ዞን  አስተዳደር ጸጥታ ሃላፊ አቶ የኔነህ ሁነኛው እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በደብረ ማርቆስ ከተማ ሲኒማ አዳራሽ ውይይት ከተደረገ በኋላ የመዛግብት ኤግዚቢሽን እና ‹Book fair› ኤግዚቢሽን  ተከፍቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽኃፍት ኤጀንሲ  እቅድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሙስጦፋ ኡስማን ለአምስት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትና አምስት የህዝብ ቤተ-መጽሃፍት  ለጎጃም በር ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ለረቡዕ ገበያ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ለደብረ ኤልያስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ቁጥራቸው 350 ሺ ዋጋቸው 450 ሺ ብር የሚደርሱ መጽሐፎችንና ለምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊ  ለአቶ ደሳለኝ አበበ አስረክበዋል፡፡ በተጨማሪም ለሞጣ፣ ለየጁቤ እና ለደብረ ማርቆስ ከተማ የህዝብ ቤተ መጽሐፍት የመጽሐፍ ስጦታዎች የተበረከቱ ሲሆን የምስራቅ ጎጃም ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ ውድላት አልማው  ተረክበዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ሌላ አካል የሆነ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ  በንግስተ ሳባ የመሰብሰቢያ  አዳራሽ  ከ24- 25 /2013 ዓ.ም  ‹‹ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውን ከመከራ ጊዜ መዛግብት፡- ጦርነት፣ ርሃብ፣  እና ወረርሽኝ›› የሚል መነሻ ጹሑፍ  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አብያተ መዛግብት  መቋቋም ተስፋና ችግሮች በሚል መነሻ ጽሁፍ ቀርቧል፡፡  በመጨረሻም  የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መዛግብት ማዕከል  የመረጃ ሃብት እና ያሉበት ችግሮች  በሚል  ረዳት ፕሮፊሰር ግዛቸው አንዳርጌ  መነሻ ጹሁፍ አቅርበዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት  ዶ/ር ይህይስ አረጉ በማጠቃለያ ሃሳባቸው እንደገለጹት ‹‹የግዕዝ ቋንቋን፣ ስነ ጽሑፍን፣ የአባቶችን ፍልስፍና መመርመር፣ ባህላችንን በማጥናት አውሮፓውያን የሰለጠኑበትን ምስጢር እናገኛለን፡፡  መነሻቸው  ኢትዮጵያ  ስለሆነች  ስለዚህ የደብረ ወርቅ ማርያም ጉብኝታችን ተመራማሪዎች ጥናትና ምርምር ለመስራት  ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል›› ብለዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የልዕቀት ማዕከልን በመለየት  በሁለት ጉዳዮች ላይ ለመስራት  ስትራቴጅክ እቅድ  እየሰራን ነው፡፡ አንደኛው  ሃገር በቀል ባህልን፣ ስነ ጽሁፍና ቋንቋን ማወቅ፣ መመርመር፣  ማስተዋወቅ፣ መጠበቅ፣ ሲሆን ሁለተኛው አርሶ አደሩ  አሁን የሚያመርተው ምርት ከእጅ ወደ አፍ ስለሆነ  ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምር ለማድረግ  ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንሰራለን፡፡

 ሌላው  የቤተ ክርስቲያናትን ቅርሶችና ሙዚየሞችን  ታሪክን በመጠበቅና የአብነት ትምህርት ቤትን  ለማጠናከርና ለመስራት  ዝግጁ ነን በማለት አክለው ገልጸዋል፡፡