ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የንጉስ ተክለሃይማኖትን ታሪክ የተመለከተ “ታሪካዊ ተዉኔት” ትያትርና መጽሃፍ ዝግጅት በቀረበ ትልመተ-ጥናት ላይ ዉይይት አካሄደ

ደ.ማ.ዩ፡- የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሐዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም አዘጋጅነት የንጉስ ተከለ ሃይማኖት (ንጉሰ ጎጃም ወከፋ) ታሪክ የሚገልጥ የትያትር ትልመተ-ጥናት መጋቢት 18/07/2013 ዓ.ም በንግስተ- ሳባ የጉባኤ አዳራሽ ዉይይት አካሄደ ፡፡

በዕለቱ በመገኝት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘደንት ዶክተር ይሄይስ አረጉ በንግግራቸዉ ‹‹የወረድነዉ ታሪካችንን መዘከር ጀግኖችን ማወደስ ያቆምን ዕለት ነዉ፣ ሀብታችንን ተሸክመን ግን መጠቀም አቅቶን ምጽዋት ስንለምን እንኖራለን፡፡ ተፈጥሮ አድልቷል ከተባለ ለጎጃም ነዉ›› ካሉ በኋላ ማህበረሰቡን በሶስት ትዉልድ ከፍለዉ አለማሳየት ሞክረዋል፡፡ እነሱም ወኔ የከዳዉ ትዉልድ፣ ባለጉልበትና ባለእዉቀት ትዉልድ፣ በመማር ላይ ያሉ ትዉልድ ናቸዉ ብለዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተፈጥሯዊ ሙሉነት ግን ሰዉ ሰራሽ ጉድለት እንዳለ ገልጸዉ በአጠቃላይ  የዚህ ዘመን ትዉልድ የተገነባዉ ባለፈዉ ትዉልድ ማንነት ነዉ በማለት ንግግራቸዉን ቋጭተዉታል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የታሪክና ተፈጥሮ ሃብት መምህር ዶክተር አዳነ ካሴ በበኩላቸዉ ታሪክን ከማስተማር አኳያ ታሪካዊ ተዉኔት ያለዉን ፋይዳ ፣ንጉስ ተከለሃይማኖት በንግስናቸዉ ዘመን ህዝቡን በማስተዳደርና የሀገር ደህንነት በማሰከበር ያደረጉትን አስተዋጽኦ ታሪካዊ ተዉኔቱን ለመስራት ስለንጉሱ ማንነት የተጠቀሟቸውን የመረጃ ምንጮች፣ ታሪካዊ ተዉኔቱ ለእይታ በሚበቃበት ወቅት ተደራሽነቱን እስከ የት ድረስ እንደ ሆነ  ለታዳሚዉ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቱ የትያትር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ዳኜ አበበ ታሪካዊ ተዉኔት ትያትር እና መጽሐፍ ዝግጅት ንደፈ ሃሳብ ላይ ጹሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በጽሁፋቸዉ  የፕሮጀክቱን ዓለማዎች፣ የፕሮጀክቱን ይዘት፣ የፕሮጀክቱ አቀራረብ ምን እንደሚመስል ለታዳሚዎች ገለጻ ካደረጉ በኋላ የዚህ ታሪካዊ ተዉኔት አዘጋጅ የሆኑት አቶ ዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳ የንጉስ ተክለሃይማኖት ታሪክ የመድረክ ቲያትር ሲሆን አምስት  ትላልቅ ገቢሮች፣አስራ ስምንት ትይንቶች፣ አስራ አንድ መቸትና የተለያዩ ግብዓቶች እንደሚኖሩት፣ በተመልካች ረገድ ወደ ቀድሞው ዘመን በመዉሰድ  የነበረዉን ባህላዊ እሴቶችን በጠበቀ መልኩ ለመስራት በቂ የሆነ ጥናትና ምርምር እንደተደረገ መረጃ ሰጥተዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሐዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዳይሬክተር  ረዳት ፕሮፌሰር ግዛቸዉ አንዳርጌ በበኩላቸዉ የባህል መስክ ለዩኒቨርሲቲዉ አንድ የልህቀት ማዕከል በመሆኑ ንጉስ ተክለሃይማኖትን ታሪክ ለመጭዉ ትዉልድ ሰንዶ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነዉ፡፡ በተዉኔት መልኩ ሲሆን ደግሞ በይበልጥ ተደራሽነት ስለሚኖረዉ ታሳቢ በማድረግ ታሪካዊ ተዉኔት የተዘጋጀበትን ምክንያት ለታዳሚዎች አስረድተዋል፡፡

የቀረበዉን ንድፈ ሃሳብ መነሻ በማድረግ ከታዳሚዎች ታሪካዊ ተዉኔቱ ታሪካዊ ክንዋኔዎችን መሰረት አድረጎ በደንብ መሰረት እንዳለበት፣ የጎጃም ታሪካዊ እሴቶችን አጉልቶ ከማሳየት አኳያ የታሪኩ ጭብጥ ሳይዛነፍ ቢቀርብ፣ ከጊዜ አኳያ ታሪኩን አጉልቶ ለማሳየት በቂ የሆነ ጊዜ ቢሰጠዉ ሀብት አፈላላጊ ኮሚቴ ቢቋቋም የሚሉ አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡

በመጨረሻም በቀረበው ንድፈ-ሃሳብ ላይ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ፕሮጀክቱ በባለቤት እንዲከታተሉት የምስራቅ ጎጃም፣ የምዕራብ ጎጃም እና የአዊ ዞኖች የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊዎች፣  ከደብረ ማርቆስ የኒቨርሲቲ፣ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲና ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲዎች አንድ አንድ ተወካዮችን  በመሰየም ወደ  ስራ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡