በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተደገፈ የፈጠራና የንግድ ስራ ሃሳቦች በሃገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው Bruh Bootcamp 2021 የንግድስራ ክህሎት ውድድር ተሸላሚ ሆነ ፡፡

ከታህሳስ 3 እስከ 18 / 2014 ዓ.ም በስራና ክህሎት ሚንስቴር አዘጋጅነት በኢትዩጵያ ኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ማዕከል አማካኝነት በደብረ ዘይት ስራ አመራር ተቋም ሲሰጥ በነበረው ስልጠና እና ውድድር ከቀረቡ አንድ መቶ/100/ የንግድ ስራ ሃሳቦች መካከል የ 5000 የአሜሪካን ዶላር ተሸላሚ የሚሆኑ 30 ሃሳቦችንና የሃሳብ ባለቤቶችን ዝርዝር ይፋ ሆኗል፡፡

ከእነዚህ 30 ተሸላሚ ሃሳቦች / ድርጅቶች /መካከል የ5ቱ ሃሳብ ባለቤቶች በቅርቡ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ስር በተቋቋሙት የቢዝነስ ማበልፀጊያ ማዕከላት አማካኝነት ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበሩ እንዲሁም ስድስተኛው ተሸላሚ ሃሳብ ከዩኒቨርሲቲያችን መካኒካልና ኢንዱስትሪያል ምህንድስና ትምህርት ቤት መምህራን የተካተቱበት በመሆኑ በተገኘው ውጤት ዩኒቨርሲቲው የተሰማውን ደስታ ይገልፃል፡፡

ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ከተመረጡትና የ200,000 ብር ተሸላሚ ከሆኑት የመጀመሪያ 10/አስር/ ሃሳቦች ሁለቱ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሄዱ ሲሆን አንዱ በቢዝነስ ማበልፀጊያ ማዕከል ድጋፍ እየተደረገለት የነበረ ሲሆን ሁለተኛው ሀሳብ ደግሞ በዩኒቨርሲቲያችን መካኒካልና ኢንዱስትሪያል ምህንድስና ት/ቤት መምህራን የቀረበ እንደነበር ይታወሳል፡፡

መሰል መነሳሳቶች በዩኒቨርሲቲያችን እየጨመሩና ዩኒቨርሲቲያችንንም ለሌሎች አጋር ድርጅቶች እያስተዋወቁልን መምጣታቸው ዩኒቨርሲቲው የሳይንስ፣የቴክኖሎጅና የስራ እድል ፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ወጣቶች ለማበረታታትና መንገድ ለመምራት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ የሚደግፉ በመሆናቸው የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ወደፊትም ቢሆን ሌሎች የዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎችም ሆነ የአካባቢውን ወጣቶች በቢዝነስ ማበልፀጊያ ማዕከላት ለመደገፍና ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለውን ቁርጠኝነት እየገለፀ ለተሸላሚዎች በድጋሚ እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት ይወዳል፡፡