የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሰራተኞች በተጋድሎ ለሚገኘው ለመከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ሀይልና ለአማራ ሚኒሻ ድጋፍ አደረገ

  • -

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሰራተኞች በተጋድሎ ለሚገኘው ለመከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ሀይልና ለአማራ ሚኒሻ ድጋፍ አደረገ

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሰራተኞች አገራችን የገጠማትን ችግር ለመቅረፍ እንደከፍተኛ ትምህርት ተቋም ማህበረሰብ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊትንና ሚና ለመወጣት የሚያስችል ውይይት አድረገዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን ሲያወያዩ

የዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማው አሸብር የውይይት መድረኩን ሲመሩ እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በግጭቱ እየተጎዳ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ለመደገፍና እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሰራተኛ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ሊያበረክተው  ስለሚገባ ጉዳይ በመወያየት የመፍትሄ አካል መሆን ስለሚገባ የተዘጋጀ ውይይት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ግርማው አያይዘውም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከእንደዚህ አይነት ችግሮች የራቁ ባለመሆናቸው በተለያየ ጊዜና ወቅት በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ሲደርሱ የነበሩ አሰቃቂና የከፍተኛ ትምህርትን የማይገልጹ ድርጊቶች ሲከሰቱ መቆየታቸውን አስታውሰው በሰሜን እዝ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ የተቃጣው ጥቃት ፈጽሞ አስነዋሪና በምንም መስፈርት ተቀባይነት የሌለው ስለሆነ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ የአማራ ልዩ ሃይልና የሚኒሻ አባላት እያደረጉት ላለው ተጋድሎና ፊልማ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የተጀመረውን የህግ ማስከበር ስራ ለመደገፍና የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት በማሰብ የተዘጋጀ የደም ልገሳና የውይይት መድረክ ነው ብለዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ ውይይቱን ሲያስጀምሩ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው እራሱን ችሎ ተነጥሎ ደሴት ባለመሆኑ አገሪቱ እየገጠሟት ያሉ ችግሮች የዩኒቨርሲቲውና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ችግር ሆኖ ከቆየ ውሎ አድሯል ስለሆነም በአገራችን የተደቀነብንን አደጋ በጋራ ለመፍታት የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በጋራ ተወይይቶ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ሀይልና ሚኒሻ ድጋፍ ለማድረግ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ  በእራሱ ተነሳሽነት የተዘጋጀ ውይይት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰራዊት በተለይ የሰሜን መከላከያ እዝ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከሰተውን የአንበጣ ወረራ ችግር ለመቅረፍ ካደረገው እንቅስቃሴ ባሻገር ከእለት ጉርሱ እየቀነሰ ትምህርት ቤቶችን፣ ጤና ጣቢያዎችን መንገዶችንና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ሲያበረክት የነበር ሲሆን በከሃዲው የህውሃት ቡድን ባልታሰበ ሁኔታ ጥቃት ተፈጽሞበታል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የአገር አለኝታ ለሆነው የመከላከያ ሰራዊትና የህግ ማስከበር ስራውን ለመደገፍ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የሚችለውን ያህል የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግና በሁለቱም በኩል ጉዳት እየደረሰባችው ላሉ ወገኖች የደም አቅርቦት ችግር እንዳይገጥማቸው ለማድረግም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ደም በመለገስ አለኝታነቱን ማረጋገጥ እንዳለበት ዶክተር ታፈረ አሳስበዋል፡፡

በውይይቱም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዩኒቨርሲቲው ሀሳብ የሚፈልቅበት ተቋም ስለሆነና ለገጠመን አገራዊ ችግር መፍትሄ የምናፈልቅበት ጊዜ በመሆኑ  ህግን ለማስከበር በተጋድሎ ላይ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ክልል ልዩ ሃይልና ሚኒሻ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከወር ደመወዙ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግና፣ ደም በመለገስ፣ ለትግል የሄደውን አርሶ አደር ሰብል በመሰብሰብ፣ መምህራን ደግሞ የጦርነቱን መነሻ ምክንያቶች ለህብረተሰቡ ለማድረስና በጦርነቱ አካባቢ እየተፈናቀሉ ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎችም ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በመጨረሻም የመከላከያ ሰራዊቱንና ሕግ በማስከበር ያለውን ቡድን ለመደገፍ ሀብት የማፈላለግ ስራ መስራት፣ በጦርነቱ ደም ለሚፈሳቸው ሰዎች ደም መለገስ፣ የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ፣ ዩኒቨርሲቲውንና አካባቢያችንን የመጠበቅ ስራና ኃላፊነትን በአግባቡ የመወጣት፣ አካባቢውን እንዲጠብቅ ማህበረሰቡን የማንቃትና ሌሎች መሰል ተግባራትን የመስራት ሃላፊነት የሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተግባር መሆን እንዳለበት ዶክተር ታፈረ አሳስበዋል፡፡ 


Search DMU

Upcoming Events

There are no upcoming events.

Partners

DMU Radio Broadcasting . . .