Category Archives: News

  • -

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በደባይ ጥላት ግን ወረዳ ናብራ ሚካኤል ቀበሌ ያስገነባውን የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት አስመረቀ

 

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ (ደ.ማ.ዩ)፡- ሰኔ 07/2014 ዓ.ም (ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዲሬክቶሬት) የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታውን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት ሞላልኝ ታምሩ (ዶ.ር) እና የደባይ ጥላት ግን ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሰዋለ መኮነን በጋራ መርቀው የከፈቱት ሲሆን በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ የዩኒቨርሲቲያችን አመራሮች፣የወረዳው የቢሮ ሃላፊዎችና የቀበሌው ኗሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በዕለቱም ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ደምሳቸው ሽታው እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲያችን 395 ሺ 500 ብር በመመደብ ለናብራ ሚካኤል ቀበሌ ማህበረሰብ የሰውና የእንስሳት መጠጥ ውኃ ገንብቶ ለማስረከብ ችሏል፡፡ ይህ የንፁህ መጠጥ ውኃ ከ300 በላይ ለሚሆኑ የቀበሌው ኗሪዎች፣ 1000 ለሚሆኑ ተማሪዎች እና ለ27 መምህራን አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልፀው በቀጣይ ይህን የንፁህ መጠጥ ውኃ በዘለቄታ ለማስቀጠል ያመች ዘንድ በአካባቢው የተፈጥሮ ሃብት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ እርክን መሰራት አለበት፣ ዛፍ መተክል አለበት እንዲህ ሲሆን ምንጮች ይጎለብታሉ የንፁህ መጠጥ ውኃው አቅርቦቱም እየጨመረ ይመጣል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ይህን ፕሮጀክት በአግባቡ እንዲሰራ ላደረጋችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኃል በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

በመጠጥ በውኃ ምርቃቱ ላይ ተገኝተዉ ሀሳባቸውን የሰጡት የናብራ ሚካኤል ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ ውበት እንደገለፁት የናባራ ሚካኤል ቀበሌ ማህበረሰብና እንስሳት ለዘመናት በውኃ እጦት ችግር ዉሥጥ ኖሯል፡፡ በቀበሌው የሚኖሩ መምህራን፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ የጤና ባለሙያዎች ተማሪዎች፣ በውኃ ጥም ሲገረፉ ኖረዋል ይህም በትምህርታቸውና በስራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም ውኃ ፍለጋ ሁለትና ሶስት ኪሎሜትር በመሄድና በአህያ በመጫን ንፅህናው ያልተጠበቀ ውኃ ሲጠቀሙ መቆየታቸውን ጠቅሰው አሁን ግን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ይህን ከፍተኛ የሆነ የውኃ ችግር በመገንዘብ ለሰውና ለእንስሳት የንፁህ መጠጥ ውኃ ገንብቶ ለማህበረሰቡ በማስረከቡ ምስጋናዬ ይድረሰው ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ ሀሳባቸውን የሰጡት መምህርት ለወየሁ መላኩ እንደገለፁት ከዚህ በፊት ውኃ ለማግኘት ብዙ ርቀት ለመሄድ እንደሚገደዱና ይህም በስራቸው ላይ ችግር ፈጥሮባቸው እንደቆየ ገልፀው አሁን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶ የንፁህ መጠጥ ውኃ ገንብቶ ለማህበረሰቡ በማስረከቡ ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ምርቃት ላይ ተገኝተው ሀሳባቸውን የሰጡት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ መልካሙ በዛብህ (ዶ.ር) እና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ድርቧ ደበበ (ዶ.ር) የዩኒቨርሲቲያችን መለያ መርሆው ”የዕውቀት አውድማ ከጮቄ ማማ“ እንደመሆኑ መጠን የዛሬ ፕሮጀክት ለዚህ መርሆዋችን አንዱ ማሳያ ተግባራችን ነዉ ብለዋል፡፡ በቀጣይም ይህ ዛሬ የተመረቀዉ ዉሃ ፕሮጀክት ለማህበረሰቡ ፍትሃዊ ተደራሽነት እንዲኖረው፣ የፀብ ምንጭ እንዳይሆንና ማህበረሰቡ የራሱ ሃብትና ንብረት መሆኑን አውቆ በአግባቡ እንዲጠቀም እንዲሁም እንዲጠብቀው ማድረግ ይኖርባችኋል በማለት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከማህበረሰቡ የወጡ ምሁራን የአካባቢያቸውን ችግር ነቅሰው በማውጣት እንዲህ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረት በማድረጋቸው፤ የአካባቢው ማህበረሰብም ለተግባራዊነቱ በጉልበትና በገንዘብ ላሳየው ተነሳሽነት ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር ሊመሰገኑ እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡  


  • -

ሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም 9ኛውን አገር አቀፍ አውደ ጥናት አካሄደ

 

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ (ደ.ማ.ዩ)፣ ሰኔ 6/2014 ዓ.ም (ህዝብ ግንኙነትና ኮምኒኬሽን ዳይሬክቶሬት) በደብረ ማርቆስ የኒቨርሲቲ የሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም 9ኛውን ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት “ባህል ለሰላም እና ለብሔራዊ መግባባት ”በሚል መሪ ሀሳብ ታላላቅ ምሁራን ፣የመንግስት አመራሮች፣ታዋቂ ደራስያን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ታላላቅ የሚዲያ ባለሙያዎች፣የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲያችን ከፍተኛ አመራሮች ፣ሰራተኞችና ተማሪዎች በተገኙበት በሀዲስ አለማየሁ የጉባኤ አዳራሽ ሰኔ 4 እና 5 በደማቅ ሁኔታ አካሄደ፡፡

This image has an empty alt attribute; its file name is pic2.jpg

በዩኒቨርሲቲያችን የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ መልካሙ በዛብህ (ዶ/ር) በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው  ባህል በሰዎችና በማህበረሰቦች መካከል መስተጋብር በመፍጠር፣ከሰዎች ጋር እንዴት በሰላም መኖር እንደሚቻል ፣በጋራ ሰርቶ እንዴት  ማደግ እንደሚቻል የሚመራ የአዕምሮ ካርታ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ይህን ቱባ ባህል ለሰላም፣ለዕድገትና ለልማት እንዲሁም በፍቅር አብሮ ለመኖር ማድረግ ሲገባን ልጆቻችንን ባለማስተማራችን፣የአንዱን ለአንዱ ባለማሳወቃችን ሀገራችን ሰላም አጥታለች፡፡ በመሆኑም በህዝባችን ዘንድ ተጠብቀው የቆዩትን ዘመን ተሻጋሪ የመቻቻልና የአንድነት እሴቶች በማጎልበት ፣ያለንን ባህል በመጠበቅ ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የአንዱን ባህል ለሌላው ማሳወቅ ከእኛ ይጠበቃል በማለት ገልፀዋል፡፡ በዕለቱ የሚቀርበው ቁልፍ ንግግር እና ጥናት ለባህል፣ ለሰላም፣ ለአብሮነትና ብሔራዊ መግባባት እንዲሆን ተመኝተው እንግዶችን እንኳን ደኅና መጣችሁ ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዝዳንት ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው  ባህል የማህበረሰቡን የሞራል ከፍታ በማሳደግ በማህበረሰቡ ዘንድ መልካም ሰብዕና እንዲጎለብት  ብሎም ሀገራዊ እሴቶች እንዲጠበቁ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ ለዚህም ዩኒቨርሲቲያችን የሞራል ልዕልና ባለቤት እና የመልካም ሰብዕና ተምሳሌት በሆኑት በዕውቁ ደራሲ ክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ስም የባህል  ጥናት ተቋም በማቋቋም የበርካታ ሊቃውንትና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ስራዎችንም ይዘክራል ብለዋል፡፡ የባህል ተቋሙ ከተቋቋመ ጀምሮ የስነ ፅሁፍ ምሽት በማዘጋጀት የተማሪዎችን የስነ ፅሁፍ ዝንባሌ በማሰደግና መልካም ሰብዕና እንዲገነቡ በማድረግ፣ቤተ መዛግብት በማቋቋም ትልልቅ ማህበራዊ እሴቶች እንዲጎለብቱ ትልቅ ስራ እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ባህል ለኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እድገትም ከፍተኛ ሚና ስላለው ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በስፋት ባህል ላይ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

This image has an empty alt attribute; its file name is pic3.jpg

የባህል ጥናቱ ተቋም ዳይሬክተር ግዛቸው አንዳርጌ (ረ/ፕሮፌሰር) የባህል ጥናት ተቋሙ የተቋቋመው የኪነ ጥበብ ልማት ስራ ለመስራት፣ ባህልን ለማጥናት፣ ለመሰነድ፣ ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ ሲሆን በውስጡ በርካታ ማዕከላትን በማቋቋም ፣ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ፣ ሀገር በቀል እውቀቶችን  በመጠቀም፣ በየወረዳዎች በመዘዋወር የግጭት አፈታትን በማስረፅ  ባህልን ፣ቅርስን ከመጠበቅና ስነፅሁፍን ከመጠበቅ አንፃር በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

This image has an empty alt attribute; its file name is pic4.jpg

በመርሀ ግብሩ የደራሲ አበረ አዳሙ አገሬን አፋልጉኝ እና ወንበዴው መነኩሴ የተሰኙ ሁለት መፅሀፍት የተመርቁ ሲሆን ደራሲዉም ከሁለቱም ቅጅዎች ከእያንዳንዱ 25 መፅሀፍት በድምሩ 50 መፅሀፍትን ለዩኒቨርሲቲያችን አበርክተዋል፡፡

ስድስት ባህል ነክ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ እንዲሁም አንኳር ንግግሮች፣ ቅኔ ፣ግጥም፣የማሲንቆና የክራር ጥዑመ ዜማዎችም ቀርበዋል፡፡  

በመጨረሻም የባህል ጥናት ተቋሙ ሊያሻስላቸውና ሊጨምራቸው የሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ በዝርዘር ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡


  • -

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን በማስገባት የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው

 

የአገራችን የግብርና ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ችግሮችን የመቋቋም አቅም የገነባ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በመንሸራትት ላይ መሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ የመቋቋም አቅም ገንብቷል የሚያሰኘው ለዘመናት ባልተቀየረ የማረሻ መሳሪያና የአስተራረስ ስልት በማደግ ላይ ያለውን የአገሪቱን ሕዝብ ቁጥር የመመገብ ግዴታውን በመወጣት ላይ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከ10 ሽህ ዓመታት በፊት በኒዮሊቲክ አብዮት ዘመን ጀምሮ የበርካታ የአዝእርትና እንስሳት ሀብት መፍለቂያ ነች፡፡ ከዚያን ዘመን ጀምሮ የአገራችን ገበሬ በትግበራ ያካበተውንና በተፈጥሮ የተሰጠውን ችሎታ በመጠቀም በዘመናዊና ቴክኖሎጂ ወለድ በሆኑ መሳሪያዎች ሳይታገዝ፣ በአንድ በኩል በየጊዜው የአፈሩ ለምነት እየቀነሰ በሌላ በኩል ቁጥሩ እየናረ የሚሄደውን ህብረተሰብ በመመገብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንንም ግዴታ ለመወጣት አርሶ አደሮች በሚያደርጉት የእርሻ መሬት ማስፋፋት የተፈጥሮ ሀብትን መመናመንና የስነ-ምህዳር መዛባትን በማያስከትሉ በዘላቂ ህልውናቸው ላይ አደጋን ሊጋብዙ ችለዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሰብል ልማትና የግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ  የግብርናውን ዘርፍ በምርምር በመደገፍ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ በያዝነው ዓመትም  የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደ አገር ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ማህበረሰቡ ለከፋ ረሀብና ችግር እንዳይገለጥ ለማድረግ  በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሊያስ ወረዳ የግዳድ ቀበሌ 255 ሄክታር እንዲሁም በማቻከል ወረዳ ከ48 ሄክታር መሬት በላይ  አስፈላጊውን ግባዓትና በማሟላት የበጋ መስኖ ስንዴን እያለማ ይገኛል ፡፡ ይህንን የበለጠ ለማሳደግና አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድርግ እየሰራ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ዘመናዊ የግብረና መሳሪያዎችን መግዛቱን አስታውቋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር እሱባለው መኩ እንደገለፁት አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የግብርና ስራ የሚከናወንበት ስለሆነና  አብዛኛውን የሀገሪቱ ምርት የሚመረትበት አካባቢ እንደመሆኑ መጠን የግብርና ስራው ግን ባለመዘመኑ የተነሳ በሚፈለገው መጠን ምርት እየተመረተ አይደለም  በዚህም የተነሳ ዩኒቨርሲቲው የራሱን ድርሻ ለመወጣት የግብርና መካናይዜሽኑን ሊደግፍ የሚችል አራት የተለያየ የፈረስ ጉልበት ያላቸው  የእርሻ  ትራክተሮችና  አንድ ኮምባይነር  በ37 ሚሊየን ብር  ግዥ በመፈፀም አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም እርሻ ስራ ተጠቃሚ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን የገለጹ ሲሆን መሳሪያዎቹ ለምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው ብለዋል፡፡


  • -

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቡሬ ካምፓስ እየተከናወኑ የሚገኙ የውስጥ ገቢ ማሳደጊያ ስራዎችና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስራዎች ጉብኝት ተካሄደ

 

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቡሬ ካምፓስ የሚያከናውናቸው የተለያዩ የልማት ስራዎችና ፕሮጀክቶችን የዩኒቨርሰቲዉ የማኔጅመንት አባላት ፣ የኮሌጅ ዲኖች እና ዳይሬክተሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች እና የአካባቢዉ ማህበረሰብ በተገኙበት መጋቢት 10/2014ዓ.ም የመስክ ጉብኝት ተደርጓል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት ቡሬ ካምፓስ ካለዉ የመልማት አቅም አንጻር በሚፈለገዉ ደረጃ ያልተሰራበት ነገር ግን ጅምሩ የሚበረታታ ስለሆነ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በዘርፉ ልምድ ካላቸው ዩኒቨርስቲዎች ልምድ በማምጣት በአካባቢዉ ያለዉን የተፈጥሮ ጸጋ በመጠቀም ወደ ስድስት የሚደርሱ በግብርናው ዘርፍ ትኩረት ያደረጉ ፕሮጀክቶችን በዘመናዊ መንገድ በመልማት ላይ መሆናቸውን በጉብኝት ወቅት ተመላክቷል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ከሆነ እነዚህ ፕሮጀክቶች በቡሬ ካምፓስ ብቻ ሳይወሰኑ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዉ ካምፓሶች ለወደፊት ይተገበራሉ ብለዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቡሬ ካምፓስ ችፍ ኤክስኪቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ዓለሙ እንደገለጹት ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቡሬ ካምፓስ አመራሮች እንዲሁም ሁሉም አካላት በመተባበር ከዩኒቨርሰቲ ከፍተኛ አመራሮች በተቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን የካምፓሱን የዉስጥ ገቢ በማሳደግና አካባቢዉን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የዶሮ እርባታ፣ የንብ ማነብ፣ የበጋ መስኖ ልማት፣ ለስጋና ሌሎች ተግባራት የሚውሉ ከብቶች ማድለብ፣ ሰው ሰራሽ ሀይቅ በመፍጠር የዝናብ ውሃን መገደብ የተለያዩ አትክልቶችና ፍራፍሬ እንዲሁም የሻይ ቅጠል ምርትን በዘመናዊ ዘዴ የማልማት ስራ የታሰቡ ፕሮጀክቶች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሰቲ ቡሬ ካምፓስ አካዳሚክ ጉዳዪች ዳይሬክተር አቶ ዉባለም ጎቤ በበኩላቸዉ የዛሬዉ ጉብኝት ዓላማዉ በከፍተኛ አመራሩ ድጋፍ ካምፓሱ ዉስጥ እየለሙ ያሉ ልማቶችን ለማሳየት እተደረገ ጉብኝት እንደሆነና ለወደፊት ታቅደዉ በካምፓሱ ወስጥ ለሚሰሩ ልማቶችን ግብዓት በመቀበል በቀጣይነት አጠናክሮ በመቀጠል ሌሎች ለዩኒቨርሲቲዉና ለካምፓሱ ገቢ ማመንጫ የሚሆኑ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ዝግጅት ላይ መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡

ከመሰክ ጉብኝቱ መልስ አጭር ግብረ መልስና ውይይትም ተካሂዷል፡፡


Search DMU

Upcoming Events

There are no upcoming events.

Partners

DMU Radio Broadcasting . . .