የደብረ ማርቆስ  ዩኒቨርሲቲ  4ኛውን  ዙር  የተማሪዎች  አምባሳደር  የእውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር አካሄደ

  • -

የደብረ ማርቆስ  ዩኒቨርሲቲ  4ኛውን  ዙር  የተማሪዎች  አምባሳደር  የእውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር አካሄደ

Print Friendly, PDF & Email

 

ዩኒቨርሲቲያችን ከተመሰረተ ጀምሮ በርካታ ተማሪዎችን በማሰልጠን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ግልጋሎቶች የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ  ይገኛል። ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለመፍጠር አልሞ እየሰራ ያለው ዩኒቨርሲቲያችን የመማር ማስተማር ስራውን የተሳካ ለማድረግ ልዩ ልዩ ተግባራትን እያከናወነም ይገኛል።

በተማሪዎች ውስጥ የተወዳዳሪነት መንፈስን በመፍጠር በትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ በማሰብ ዩኒቨርሲቲው ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን በመመልመል የእውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር እያዘጋጀ ለተማሪዎች በአምባሳደርነት የክብር ማዕረግና ሽልማት እየሰጠ ይገኛል።

የ2015 ዓ.ም የ4ኛው ዙር የተማሪዎች የአምባሳደር  የእውቅናና ሽልማት መርሐ ግብርም መጋቢት 16 እና 17 ቀን /2015 ዓ.ም የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ፣ ዲኖች ፣ ዳይሬክተሮች ፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተገኙበት በዋናው ግቢ እና በቡሬ ካምፓስ በደማቅ ሁኔታ ተካሄዷል።

This image has an empty alt attribute; its file name is Ambassador-2.jpg

በዚህ የሽልማትና የእውቅና መረሐ ግብር  ላይ ተገኝተው ለተሸላሚ ተማሪዎች መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ.ር ይኼይስ አረጉ እንደገለፁት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ያሳለፍናቸው አያሌ ዘመናት እውነታ እንደሚያመለክተው በየጊዜው የነበረው ትውልድ ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታው ያቀረበለትን ገፀ በረከቶች እየተጠቀመና የሚችለውን ያህል በማደረግ ታሪካዊ ግዴታውን እየተወጣ፤ ቀደም ሲል ያልተመለሱ ጥያቄዎችንና ያልተፈቱ ችግሮችን ደግሞ እየመለሰ፣ እየፈታና እያቃለለ እንዲሁም የታሪክ ቅብብሎሹን እያሳለጠ እንደመጣ ይታመናል ያሉት ዶክተር ይሄይስ ይህ የሚያሳየው ደግሞ የየዘመኑ ትውልድ ከቀደሙ አባቶች ወይም ከሚኖርበት ዓለም የሚቀርብለት ወርቃማ ዕድል እንዳለ ሁሉ የሚጋፈጠው ዕልህ አስጨራሽ ውድድርና ትግልም የሚጠብቀው መሆኑን ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በአፅናፉዊ ትስስር የፍልስፍና ማዕቀፍ እየተመራ ያለው አሁን የምንኖርበት የ21ኛዉ ክፍለ ዘመን የሁኔታዎች ተለዋዋጭነት የበዛበት፣ ከፍተኛ ስጋትና ጥርጣሬ የነገሰበት፣ ለውጥ የፈጠነበት፣ የሰው ልጅ ፍላጐት ከጊዜ ጊዜ እየተውሰበሰበ የመጣበት፣ ሳይንስና ዲጂታል ቴክኖሎጂ እየረቀቀና እየመጠቀ የመጣበት እንዲሁም ውድድር የከረረበት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

ለዘመናት በተፈጥሮ ላይ ተንጠልጥሎ የቆየው የሰው ልጆች የአኗኗር ሁኔታም የሳይንሳዊ ዕውቀትን ድጋፍ የጠየቀበት ዘመን ላይ የምንገኝ መሆኑንም መገንዘብ እንደሚገባም ያስገነዘቡት ም/ፕሬዚደንቱ  በእንደዚህ ዓይነት ፍፁም ተገማች ያልሆነ ዓለም ውስጥ የሚኖርና ለስኬት፣ ለጥሩ ውጤትና ለተሻለ ተጠቃሚነት የሚተጋ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ማህበረሰብ ያስቀመጠውን ራዕይ በተፈለገው ደረጃ ለማሳካት ይችል ዘንድ የአስተሳሰብም ሆነ የአሰላለፍ ቅኝቱ ሁልጊዜም በተፎካካሪነት መንፈስና በሳይንሳዊ ዕወቀት፤ በጥበብና በማስተዋል ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ይታመናልም ሲሉ ገልፀዋል፡፡

አሁን ትምህርቱን በመከታተል ላይ ያለው ወጣቱ ትውልድ ከላይ የተዘረዘሩትን ወሳኝ የዘመን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል ሳይንሳዊ፣ ስነ ልቦናዊና አካላዊ ዝግጁነት እንዲኖረው አድርጐ ማስተማር ፣ መምከር ፣ ማበረታታትና ማብቃት እንዲሁም የተለየ ጥረትና ትጋት ለሚያሳዩና አብላጫ ወጤት ለሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ዕውቅና መስጠት የትምህርት ተቋማት ታሪካዊ ሃላፊነት መሆኑን መገንዘብና መተግበር ለሃገርም ለትውልድም አሰተወጽኦው ከፍተኛ መሆኑንም በአፅንኦት ገልፀዋል።

ይህን ጉዳይ በጊዜ የተረዳው የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎቹን የተፎካካሪነትና የተወዳዳሪነት ስሜት ከፍ ለማድረግና አቅማቸውን አሟጠው ለትምህርታቸው ብቻ እንዲጠቀሙና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ባለው ፍፁም ዕምነትና ቁርጠኝነት በየዓመቱ በአጠቃላይ 3.75ና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን እንዲህ በደመቀ ሁኔታ በፕሬዝደንት አምባሳደርነት ማዕረግ ዕውቅና በመስጠት፣ በመሸለምና በማበረታታት ረገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መሆኑን ስንገለፅ ታላቅ ክብር ይሰማናልም ሲሉ አክለዋል።

ዛሬ ዕውቅና የምንሰጣቸው ጀግና ፣ ታታሪና አሸናፊ ተማሪዎቻችን ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም በጠንካራ የውድድር ስሜትና ታላቅ ተስፋ ታጅበው ሲማሩ፣ሲያጠኑና በትምህርታቸው ሲበረቱ የቆዩ በመሆናቸው ባስመዘገቡት አብላጫ ውጤት ምክንያት በመሆኑ እነዚህ ባለሙሉ ተስፋ ልጆች ከራሳቸው የመንፈስ እርካታ በላይ ያሳደጓቸው ቤተሰቦችና ያስተማሯቸው መምህራን የሚሰማቸው ክብርና ኩራት በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፡፡

በመጨረሻም ባለፉት ተከታታይ ሴሚሰተሮች የትምህርት ጊዜያችሁን በአግባቡ በመጠቀማችሁ፣ የተሸለ ጥረት በማድረጋችሁና ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባችሁ ዛሬ ዕውቅናና ሽልማት ስትቀበሉ ቀጣዩን የመማር ጉዞ ከዛሬው በላቀ ወጤት ለመዝለቅ ሞራልና ወኔ እያገኛችሁና ወደፊት ለመንደርደር የሚያሰችላችሁን ጉልበት እያጠራቀማችሁ መሆኑን በመተማመንና ወደፊት በሚጠብቃችሁ ዲጂታል ውድድር ውስጥ ድልን በመቀዳጀት መሆን የምትፈልጉት ጫፍ ላይ እንደምትደርሱ እርግጠኛ በመሆን ቀሪ የትምህርት ጊዜያችሁና አጠቃላይ ህይወታችሁ ስኬታማና ዉጤታማ እንዲሆን ከልብ በመመኘት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

This image has an empty alt attribute; its file name is Ambassador3.jpg

በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ለተማሪዎች መልዕክት ያስተላለፉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ- ልቦና መምህርትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት  ማስተዋል መኮንን (ዶ.ር ) እንደገለጹት በዚህ የተማሪዎች የሽልማትና ዕውቅና ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉ በመጋበዛችው ዩኒቨርሲቲውን አመስግነው ተማሪዎችም በወጣትነት ጊዜ በርካታ ፈተናዎችና ውጣውረዶች እንደሚያጋጥማቸው ገልጸው ተማሪዎች ይህንን ትግል አሸንፈው ለዚህ ውጤት በመብቃታቸው  ሊኮሩ እንደሚገባቸው ጠቅሰው ነገሮችን በሰከነ አዕምሮ ዓላማቸውን ማሳካት እንዳለባቸው በቀጣይም ይህንን ጥንካሬ የበለጠ ማስቀጠል እንዳለባቸው እና የራሳቸውንም ተሞክሮዎች በማንሳት ለተማሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

This image has an empty alt attribute; its file name is Ambassador4.jpg

በዚህ ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ እውቅናና ሽልማት ከተደረገላቸው ተማሪዎች  መካከል ከኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ትዕግስት ታረቀኝ 3.96፣ ብሩክ አወቀ 4፡00 እና ደረጀ ወርቄ 4፡00 በማስመዝገብ ዘመናዊ ታብሌት ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ሽልማቱም በትምህርታችን ላይ ትኩረት እንድናደርግ ያነሳሳናል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው እንዲህ ዓይነት ፕሮግራም በማዘጋጀት ለተማሪዎች እውቅናና ሽልማት ማድረጉ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎችም መነቃቃትን፣ መነሳሳትን ይፈጥራልና ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ሲሉም አክለዋል። በርካታ ጫናዎችና ፈተናዎች ቢኖሩም እንኳ የአላማ ጽናትና ጥንካሬ ካለ ዓላማቸውን ማሳካት እንደሚችሉ ገልጸዋል። ይህ ውጤትም የቤተሰቦቻቸው ፣ የመምህሮቻቸው እና የጓደኞቻቸው ውጤት እንደሆነ ፤ በእነሱ ድጋፍና ጥረትም ለዚህ በቅተናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡


Search DMU

Upcoming Events

There are no upcoming events.

Partners

DMU Radio Broadcasting . . .