ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የግዕዝ ቋንቋ ልማት ስትራቴጅክ እቅድ አረቀቀ

  • -

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የግዕዝ ቋንቋ ልማት ስትራቴጅክ እቅድ አረቀቀ

Print Friendly, PDF & Email

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ወልቂጤ ዩኒቭርሲቲና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የግዕዝ ቋንቋ ልማት ስትራቴጅክ እቅድ አረቀቁ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ግዛቸው አንዳርጌ ስለ ስትራቴጅክ ዕቅዱ ሪፖርት ሲያቀርቡ

በዩኒቨርሲቲው የሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ግዛቸው አንዳርጌ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በክቡር ሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ስር በርካታ ተግባራትን እየሰራ መሆኑን ገልጸው የግእዝ ቋንቋ ልማት ስትራቴጅክ ዕቅድ መቀረጹ ለተቋሙ በርካታ ግብአቶችን የሚያስገኝ መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው በግእዝ ቋንቋ ስነ-ጽሁፍና በሙዚቃ ሁለት ስርአተ ትምህርት መቅረጹን ገልጸዋል፡፡

በባህልና ቱሪዝም አስተባባሪነት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሲካሄድ የነበረው የግእዝ ቋንቋ ልማት ስትራቴጅክ እቅድ ዝግጅት ከኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቋንቋ ልማት ባለሙያዎች፣የተለያዩ ዩኒቭርሲቲዎች ምሁራን በጋራ በተደረገ ውይይት ከውይይቱ በተገኘ አጠቃላይ ግብአት መሰረት ስትራቴጅክ እቅዱ መቀረጹን ረዳት ፕሮፌሰር ግዛቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ገነት ደጉ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው የሚገኙ የመልማት አቅሞችን በመለየት በክቡር ሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ስር በቋንቋ፣ ታሪክ፣ባህልና ቅርስ ጥበቃ ላይ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ገነት ደጉ የግእዝ ቋንቋ በአገራችን ቀዳሚው ቋንቋ መሆኑን አስታውሰው ብዙ ታሪኮች፣እውቀቶች፣ፍልስፍናዎችና ሌሎች ነገሮችን እንደማህደር የያዘ ቋንቋ በመሆኑ ቋንቋውን ለማበልጸግ በየቦታው የሚሰራውን ስራ ለማደራጀት መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት ቋንቋውን በመታደግ ወደ ቀድሞው ክብራችንና እድገታችን መመለስ ይገባል ብለዋል፡፡

በመሆኑም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የግእዝ ቋንቋ ለሀገር ልማት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ በቀጣይ በሀገሪቱ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት በመተግበር በቋንቋው ተመዝግበው የሚገኙ የካበቱ እውቀቶችን ለሀገር እድገት በአግባቡ ለመጠቀምና ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል ባለድርሻ አካላትን በማስተላለፍ የግእዝ ቋንቋ ልማት ስትራቴጅክ እቅድ ተቀርጧል፡፡

የግእዝ ቋንቋ ልማት ስትራቴጅክ እቅድ መቀረጹ የግእዝ ቋንቋ በስነ-ጽሁፍ ሀብትነቱ የሀገሪቱን ቀደምት ታሪክ፣ፍልስፍና፣ስነ-ፈለክ፣ስነ-ምህዳርና ሀገረ-ሰብአዊ እምነቶች፣ ቅርሶች፣ልማዶች፣ጥበባት፣መድሀኒቶችና ሌሎችን የእውቀት ክምችቶችን በመጠቀም የምንመራበት ትልቅ አቅም ያለው ጥንታዊ ሀብት በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ተገልጧል፡፡

የግእዝ ቋንቋ ልማት ስትራቴጅክ እቅድ በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ የተለያዩ ጽሁፎችን ለመመርመርና ለመጠቀም የሚያስችል እውቀት መፍጠር፣በግእዝ ቋንቋ የሚገኙትን የተለያዩ ሀገር በቀል እውቀቶችን ማሰባሰብ፣መሰነድ፣ የግእዝ ቋንቋን በተመለከተ የመማር-ማስተማሩን ሂደት በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲካሄድ ማድረግና የግእዝ ቋንቋ የያዛቸውን ሀብቶች ተጠቅመን የቀደመ ማንነትን መመለስ የግእዝ ቋንቋ ልማት ስትራቴጅክ እቅዱ ግቦች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የእዚህ ስትራቴጅክ እቅድ ዓላማዎችም ግእዝን መግባቢያ ቋንቋ ማድረግ፣የግብረገብ ትምህርት በግእዝ ቋንቋ በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረግ፣የግእዘ ቋንቋ ወጥነት ያለው ስርዓተ-ትምህርት ማዘጋጀት፣የአብነት ትምህርት ቤቶችን በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ማእከል በማደራጀት ባህላዊ የሆነውን የትምህርት አሰጣጥ ከዘመናዊ ትምህርት አሰጣጥ ጋር በማቀናጀት ማቅረብ፣የግእዝ ቋንቋን ማህበረሰቡ እንዲጠቀመው ለማድረግ ግንዛቤ መፍጠር፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ግዕዝ ቋንቋ ላይ አለም አቀፋዊ ጥናቶችን የሚያዘጋጅ እራሱን የቻለ ተቋምና የምርምር ውጤቶች የሚታተሙበት የምርምር መጽሄት ማዘጋጀት፣ስለ ግእዝ ቋንቋ ማብራሪያዎችንና አስተያየቶችን በመስጠት በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር በእያንዳንዱ ተቋም ድረ-ገጾችንና የፌስቡክ ገጾችን ማዘጋጀትና የተለያዩ አውደ ጥናቶችን ማካሄድናቸው ተብሏል፡፡

በግእዝ ቋንቋ ልማት ስትራቴጅክ እቅዱ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትም አውደ ጥናት ማካሄድ፣ ስነዳ፣ የቋንቋ ሀብት ማበልጸግና ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በተያያዘም አዲስ አበባ ዩኒቭርሲቲ፣ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣መቀለ ዩኒቭርሲቲ፣ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ወሎ ዩኒቨርሲቲና አክሱም ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓት የግእዝ ቋንቋ ትምህርት እየሰጡ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና ደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ የግእዝ ቋንቋን ለማስተማር በሂደት ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡


Search DMU

Upcoming Events

There are no upcoming events.

Partners

DMU Radio Broadcasting . . .